ቀጥታ፡

የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ነሐሴ 15/2010 በታንዛንያ እየተካሄደ ባለው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ ይካሄዳሉ። በ2011 ዓ.ም በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ክፍለ አህጉሩን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የማጣሪያ ጨዋታ እየተካሄደ ይገኛል። ዛሬ ከቀኑ 11 ሰዓት ከምድብ አንድ አዘጋጇ ታንዛኒያ ከሩዋንዳ ጋር በቻማዚ ስታዲየም ትጫወታለች። ምድቡን ታንዛኒያና ሩዋንዳ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፉ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኖቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ከምድቡ አንደኛ ሆኖ የሚያልፈውን ቡድን ይወስናል። በዚህ ምድብ ሶማሊያ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ የምድቡ ጨዋታዎች በአራት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል እየተካሄዱ ሲሆን ብሩንዲ በሦስት ጨዋታዎች አንዱን አሸንፋ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ሱዳን በሦስቱም ጨዋታዎች ተሸንፋ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች። ነገ በቻማዚ ስታዲየም በምድብ አንድ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ኡጋንዳ ከጅቡቲ፣ ከቀኑ 11 ሰዓት ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ይጫወታሉ። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ነገ የሚያደርገውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ከምድቡ አንደኛ በመሆን ከሩዋንዳና ታንዛኒያ ጨዋታ ሁለተኛ ሆኖ ከሚጨርሰው ጋር የሚገናኝ ይሆናል። ኢትዮጵያ ምድቡን በዘጠኝ ነጥብ ስትመራ ኡጋንዳና ኬንያ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። እስከ አሁን በሴካፋ የማጣሪያ ውድድር በተደረጉ 13 ጨዋታዎች 63 ግቦች ከመረብ ያረፉ ሲሆን ውድድሩ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም