የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት 105 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት 105 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረገ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመሻገር እየተደረገ ባለው ዘመቻ ሰራዊቱ ኢትዮጵያን ለማዳን በጀግንነት እየተፋለመ ይገኛል።
የአገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅና ሉአላዊነቷንም ለማስከበር ህዝቦች ሰራዊቱን በመደገፍና የአካባቢያቸውንም ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።
በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለሰራዊቱ ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድርጓል።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ፤ "አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ እየተደረገ በሚገኘው የህልውና ዘመቻ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት እና የክልል ጸጥታ ሃይሎች ጎን በመቆም ህዝቡ ድጋፉን እያሳየ ይገኛል ብለዋል።
በየአካባቢው የሚገኘው ማህበረሰብ ለሰራዊቱ ደጀን መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጡ ተግራባትን በተከታታይ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ክፍለ ከተማው እስካሁን ለሰራዊቱ በሁለት ዙሮች ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ዘመኑ በመጀመሪያው ዙር 106 ሚሊዮን ብር፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 186 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በዛሬው እለት ደግሞ ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ እንዲሁም በውጭ ደጋፊዎቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጦርነት በድል ለመወጣት በጋራ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
በሀልውና ዘመቻው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ነው ያሉት።