ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ክልል ለበረራ የደህንነት ስጋት አለበት ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ሃሰት ነው

ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአየር ክልል ለበረራ ስጋት አለበት ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ሃሰት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ በሰጡት መግለጫ "አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በማደናገር ላይ ይገኛል" ብለዋል።

በዚህም አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም ዜጎች ስጋት ውስጥ እንዲገቡ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ "ይህ እንቅስቃሴው መቼም አይሳካለትም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ባደረገው ቅኝት የኢትዮጵያ አየር ክልል እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሸባሪው ቡድን በሚያናፍሰው የሃሰት ወሬ በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ የማህበረሰብና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ስራቸውን አቋርጠው እንደነበር የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሰባት የማህበረሰብና 19 ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ስራ አቋርጠው እንደነበር ጠቁመዋል።

"ከእነዚህ ውስጥ ለሶስቱ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ አሁን ሁሉም መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸውን ጀምረዋል" ብለዋል።

"መንግስት የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየሰራ ይገኛል" ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ የኮቪድ-19 ክትባት በዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዘመቻውም 7 ሚሊዮን ሰዎች ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም