ቀጥታ፡

ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን እንደግፋለን - ታዋቂ አትሌቶች

አዲስ አበባ  ነሀሴ 15/2010 በመዲናዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና ለተቸገሩ  የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ታዋቂ አትሌቶች ተናገሩ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎ ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ከታዋቂ አትሌቶችና የእግር ኳስ ባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርጓል። ኢትዮጵያን በተለያዩ የአትሌቲክስ  ውድድሮች  ሰንደቋን ከፍ በማድረግ ሲያስጠሩ የነበሩና እያስጠሩ ያሉ አትሌቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት አርዓያ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የአረጋዊያን መኖሪያ ቤት ማደስ፣ አካባቢን ማጽዳትና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች መካከል ይገኙበታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደተናገረው በበጎ ፍቃድ የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። መዲናዋን በማጽዳትና ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲኖራት ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል። በሚያስፈልገው የበጎ አግልግሎት ሁሉ ለመሳተፍና ለመደገፍ  ዝግጁ መሆናቸውን የሚናገረው ደግም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አትሌት ስለሺ ስህን ነው። እንደ እርሱ ገለጻ በማህበሩ ቀደም ሲል በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚያደረገው እንቅስቃሴ ተካፋይ እንደነበርና በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግሯል። ይሁን እንጂ የከተማው ከንቲባ በመዲናዋ ያለውን የአትሌቶች እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት የልምምድ ስፍራዎች ምቹ ሆነው እንዲሰሩ ጠይቋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ አቅም በፈቀደ መጠን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጾ በቆሻሻ የተሞሉ የአትሌቶች መሮጫ ሥፍራዎችን ማጽዳትና የመሮጫ ትራኮችን በፖርኮች ውስጥ እንዲዘጋጁ እቅድ እንዳለውና የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ይገልጻል። "የኢትዮጵያ ህዝብ ለአትሌቶች ክብር እንደሚሰጠው ሁሉ እኛም ለህዝቡ  ከአካባቢያችን በመጀመር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ለወጣቱ አርዓያ ልንሆንና የተስፋን መንገድ መጥረግ ይጠበቅብናል" የሚለው ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማሪያም ነው። አህትማማች አትሌቶች ገንዘቤና እጅጋየው ዲባባ በበኩላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት እድሉ ተመቻችቶ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው አትሌቶች ያነሷቸውን ጥያቄዎች በመቀበል አብሮ ለመስራት ሙሉ በሙሉ እንደሚስማሙባቸው ገልጸዋል። በመዲናዋ ጉዳይ ከሚመለከተው አካል በመመካከር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንና አብሮ ለመስራትም በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል። አገሪቷ በአትሌቲክሱ ዘርፍ በርካታ ገድሎች እያስመዘገበች መሆኑን ጠቁመው ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ እስካሁን ብዙ ጀግኖች አትሌቶች መፈጠራቸውን አስታውሰው  የታሪክ  ፍሰቱን ትውልዱ ማስቀጠል እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።   ምክክሩ በአዲስ አበባ ከተማ አዘጋጅነት "የአዲስ ተስፋ ቀመር ጥላቻን መቀነስ፣ ያለንን ማካፈል፣ይቅርታን ማብዛት፣ በፍቅር መደመር" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሄዷል። በአሁኑ ወቅት ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ በወጣቶች አማካኝነት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሰፊው እየተሰጠ ሲሆን አዲስ አበባም  የተለያዩ የበጎ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የዘንደሮው የሚለየው ደግሞ ለበርካታ ዓመታት አገሪቱን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ ግልጋሎት የሰጡና እየሰጡ ያሉ ታዋቂ ሰዎችን በማካተት የሚሳተፉበት በመሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም