ቀጥታ፡

አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ያለውን ጣልቃገብነት እና ጫና እስከመጨረሻው እንታገላለን

ህዳር 11/2014 ( ኢዜአ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጣልቃገብነት እና ጫና እስከመጨረሻው እንታገላለን ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ዜጎች ምክር ቤት አስታወቀ።

"ለሦስት ሺህ ዓመታት በነፃነት ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ በታሪኳ በሕልውናዋ ተደራድራ አታውቅም፤ ዛሬም አትደራደርም" ብሏል ምክር ቤቱ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዲያቆን ዮሴፍ ጥሩነህ "ኢትዮጵያን ከጥንትም ጀምሮ ጠላት ተለይቷት አያውቅም" ይላሉ።

የአሁኑን የጠላት ዘመቻ የሚለየው ግን ኢትዮጵያ ላይ የተነሳው ጠላት አንድ አገር ሳይሆን ግማሽ ዓለም የሚሆነው አሜሪካ መራሹ የምዕራቡ ዓለም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለመነጠል በሚቆጣጠሯቸው መድረኮች ሁሉ ማሳጣት፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫናን ጨምሮ ወታደራዊ ጣልቃገብነት እናደርጋለን እስከማለት መደረሱን አውስተዋል።

በቅርቡም በሚዲያዎቻቸው ይህንኑ ሃሳብ ሲያንጸባርቁ እንደነበር አንስተው፤ ምዕራባዊያኑ አገራት በዝምታ ከታለፉ ኢትዮጵያ ላይ የሚችሉትን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል።

ዲያቆን ዮሴፍ ጥሩነህ የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት፣ የተፈጥሮ ሐብትና ለቀይ ባህር ያላት መልክዓ ምድራዊ ቅርበት አሜሪካን ጨምሮ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነቷ በሃያላኑ ዘንድ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ቀንድ አገራት በትብብር የማልማትና ከጥገኝነት የማላቀቅ አቅም እንዳላት በመረዳት፤ ምዕራባዊያኑ ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆነ መንግስት ለቀጣናው ፍላጎታቸው ስጋት እንደሆነ ያምናሉ ብለዋል።

ለዚህም ተላላኪ ስርዓት መፍጠር የሁልጊዜም ጥረታቸው መሆኑን፤ አሜሪካም ከ30 ዓመታት በፊት ህወሓትን ወደ ስልጣን እንዲመጣ ማድረጓ ፍላጎቷን ለማስፈጸም ተላላኪ ቡድን ስለሆነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህወሓት ሲፈጽም የነበረውን አፈና በመቃወም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ኤች.አር 28 የተሰኘውን የሕግ ማዕቀፍ እንድትደነግግ ቢገፋፉም ከራሷ ጥቅም ውጭ የማይዳዳት አሜሪካ ግን ትኩረት አልሰጠችውም ሲሉ አስታውሰዋል።

ይሁንና በሕዝብ ማዕበል ተገፍቶ ከስልጣን የተወገደውን የሽብር ቡድኑን ህወሓት ወደ ስልጣን ለመመለስ የፈለጉት የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ተላላኪ እንደማይሆን በማረጋገጣቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

በጥቁሮች መብት ረገጣ የምትታወቅው አሜሪካ በሠብዓዊ መብት ብታሳብብም በኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ሁለንተናዊ ጫና እና ጣልቃገብነት ግን ከግል ጥቅሟ የመነጨ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

አሜሪካ በሌሎች አገራት ላይ እንደፈጸመችው ሁሉ ፍላጎቷን ለማሳካት በምትዘውራቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ብዙ ጥረት እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል።

ፍላጎቷን ለመጫን ከምትጠቀምባቸው መካከል ከመከላከያና ደህንነት ተቋማቷ በተጨማሪ የዓለምን ማኅበረሰብ የሚያደናግሩ መገናኛ ብዙሃን ቁልፍ መሳሪያዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ለይስሙላ ነጻ ሚዲያ ይባል እንጂ ከአሜሪካ ቁጥጥርና ፍላጎት ውጭ የሆነ የትኛውም ሚዲያ እንደሌለም ገልጸዋል።

በኢራቅ ላይ የጥፋት መሳሪያ ተገኘ ተብሎ ለተፈበረከው ሀሰተኛ መረጃ በአሜሪካ ከሚገኙ ከ200 በላይ ሚዲያዎች ውስጥ ከአንድ ሚዲያ በቀር እውነቱን ያጋለጠ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

ይህ በኢራቅ ጉዳይ ዕውነቱን ያወጣ የሚዲያ ተቋም በአሜሪካ መንግስት እንዲጠፋ መደረጉን፤ ዛሬም በኢትዮጵያ ጉዳይ የዘመቱ ሚዲያዎች የሚያወጡት የውሸት ዝናብ ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮ-አሜሪካዊያን ሀሰተኛ መረጃዎችን በመቃወም ተጨባጩን እውነታ ለማስረዳት ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጽሁፎችን ቢልኩም ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያጣላናል በሚል እንዳላወጡትም ተናግረዋል።

አሜሪካ ከ30 ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቸኛ ልዕለ ሃያል አገር ባትሆንም ዛሬም ግን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማደናገር በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ሁለንተናዊ ጫና ታዳጊዋን ኢትዮጵያ እንደሚጎዳት ይታወቃል ይላሉ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ።

ነገር ግን ለ3 ሺህ ዓመታት በነጻነት የቆየችው ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ተደራድራ አታውቅም፤ ዛሬም እንደማትደራደር ልቿ ለምዕራባዊያን መንግስታት እያስረዱ ነው ብለዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካ እያደረገች ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም መልከ ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአብነትም ሠላማዊ ሠልፍ በማድረግ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እና ሎቢስትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን በመቅጠር የኢትዮጵያን ዕውነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ እያደረጉት ያለውን ንቅናቄ ጠቅሰዋል።

ምንም እንኳን ሚዲያዎቹ የኢትዮጵያን ዕውነቶች ለማስተጋባት ፈቃደኛ ባይሆኑም ኢትዮ-አሜሪካዊያን ግን በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በትዊቲር ከፍተኛ ተዕጽኖ መፍጠር ችለናል ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርጓቸው የነበሩ በርካታ እንቅስቃሴዎችና ውሳኔዎችን እስከመቀየር፤ የሚዲያዎችን ዘገባም እርማት እስከማድረግ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

በአሜሪካ በሚካሄዱ ምርጫዎች የወቅቱን መንግስት የሚመራውን የዴሞክራት ፓርቲ ባለመምረጥ ዘመቻ በማድረግ በድምጻቸው እየቀጡ ስለመሆኑና ወደፊትም ይህን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ሊቢያ እና ኢራቅን ጨምሮ በርካታ አገራት በአሜሪካ ጣልቃገብነነት ሲንኮታኮቱ በአሜሪካ የሚኖሩ ዜጎቻቸው መቃወምን እንደፈሩ ገልጸዋል።

ኑሯችንን በአሜሪካ ያደረግን ኢትዮጵያዊያን ግን ያለ ምንም መሸማቀቅና ፍራቻ እስከመጨረሻው ድረስ ለኢትዮጵያ ሕልውና ቆርጠን እንታገላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም