የዞኑ ሴቶች በግንባር ተሰልፈው አሸባሪውን ህወሓ በመደምሰስ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዞኑ ሴቶች በግንባር ተሰልፈው አሸባሪውን ህወሓ በመደምሰስ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተዘጋጅተዋል
ፍቼ ህዳር 10/2ዐ14 በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች ከስንቅ ድጋፍ ባሻገር በግንባር ተሰልፈው አሸባሪውን ህወሓትና ተላላኪዎቹን በመደምሰስ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ መዘጋጀታቸውን ገለፁ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ13 ወረዳዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመደገፍ ሁለተኛ ዙር የስንቅ ዝግጅት ሥራ ተጀምሯል።
በዞኑ ሴቶች በተጀመረው ሁለተኛ ዙር የስንቅ ዝግጅት ሥራ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደረቅ ምግብ ለማዘጋጀት መታቀዱ ተመላክቷል።
በስንቅ ዝግጅቱ ከተሳተፉት መካከል የግራር ጃርሶ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኛ ወይዘሮ ፀሐይ ተካ እንዳሉት፣ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው።
የሀገርና የህዝብ ደህንነት እንዲረጋገጥ የጀመሩትን ድጋፍ ከማጠናከር ባለፈ አሸባረውን ህወሓትና ተላላኪውን ሸኔን በግንባር ለመፋለም መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
"የኢትዮጵያ እናቶች ታሪክ የሚያሳየው ጠላት ሲመጣ በጋራም ሆነ በተናጠል መዝመት፣ ወገንን ማበረታታትና በጦር ሜዳ የተጐዱ ወገኖችን ማከም በመሆኑ እኛም የወላጆቻችንን ታሪክ እንደግማለን" ብለዋል።
"አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ንጹሃንን እንዲገድልና የሀገር ሃብት እንዲያጠፋ ተጨማሪ እድልና ቦታ መስጠት የለብንም" ያሉት ደግሞ የግራር ጃርሶ ወረዳ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት መስፍን ናቸው።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷና ክብሯ እንዲጠበቅ ግንባር ድረስ በመዝመት የጀግኖች እናቶችና አባቶችን አኩሪ የድል ታሪክ ለመድገም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዘመቻ ምግብ ዝግጅት ዋና አስተባባሪ ወይዘሮ መዝገቤ አበበ እንደገለጹት፣ ህብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያዳረገ ነው።
አስተባባሪዋ እንዳሉት በስንቅ ዝግጅቱ 1ዐሺህ የዞኑ ሴቶች ያለማንም ቀስቃሽ በራሳቸው ተነሳሽነት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ሴቶቹ በየአካባቢያቸው ገንዘብ በማዋጣትና በጉልበታቸው ጭምር በመሳተፍ በህልውና ዘመቻው የደጀንነት ሚናቸውን እያረጋገጡ መሆኑንም ገልጸዋል።
የግራር ጃርሶ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ኢድኣ እንዳሉት ሴቶች ለሀገር አሸባሪውን ህወሓት በግንባር እየተፋለሙ ለሚገኙት ጀግኖቻችን እያደርጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ከእዚህ ቀደም የዞኑ ሴቶች ልጆቻቸውን መርቀው ወደ ጦር ግንባር ከመላክ በተጨማሪ በርካታ ሰንጋ በሬዎችና ሙክት በጐችን ለሠራዊቱ መለገሳቸውንም አስታውሰዋል።