ቀጥታ፡

ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱ ያሉት ጫና የአፍሪካ ቀንድን ለመቀራመት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ነው

መቱ ፤ ሕዳር 10 /2014 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን በሰብዓዊ መብት ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱ ያሉት ጫና ለነሱ ተላላኪ መንግስት እንዲኖርና የአፍሪካ ቀንድን ለመቀራመት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ነው ሲሉ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ።

ባለፉት 27 ዓመታት አሸባሪው ሕወሓት ሀገረ መንግስቱን ሲመራ በዜጎች ላይ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም  ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነኝ የሚል አንድም የውጭ አካል የጠየቀው እንዳልነበረ ይታወቃል።

ይኸ ደግሞ ጉዳያቸው ከሰላም ማስከበርና ሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመከላከል አጀንዳ እንዳልሆነም በግልፅ የሚያመላክት መሆኑን ነው ምሁራኑ ለኢዜአ የገለጹት።

በዩኒቨርሲቲው የውጭ ቋንቋ መምህር  ዶክተር በድሉ ተካ እንደሚሉት፤አሸባሪው ሕወሓት በተለይም  ከነርሱ ተልዕኮ ተቀብሎ ለጥቅማቸው ይሰራ የነበረ ተላላኪያቸው እንደነበር   የሚያረጋግጠው ዛሬም ዜጎችን በግፍ እየፈጀ ለዚሁ ቡድን ወግነው መቆማቸው ነው።

የኢትዮጵያ መረጋጋትና መበልጸግ ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ተነሳሽነትን የሚፈጥር እንደሆነ የገለጹት ምሁሩ፤ በዚህም  ጥቅማቸው እንደሚቀንስ ስለተረዱ  የሚያደርጉት ጫና አንድም ከስጋት የሚመነጭ ነው ይላሉ።

በተለይም የአገሪቱ  "የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካዊያን" የሚለው አጀንዳ በምዕራባዊያን ግልጽ ቅናትን ፈጥሯልም ብለዋል።

የሕወሓትን የአጥፊነት ተግባር እያወቁ ዛሬም ከቡድኑ ጋር ተባብረው ሀገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችም በማንኛውም መስፈርት ማንኛውንም ብሔር የማይወክሉና ስለሀገር ደንታ የሌላቸው የራሳቸው ጥቅም ፈላጊዎች ናቸው የሚሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው  የጋይዳንስ ሳይኮሎጂ መምህር  ረዳት ፕሮፌሰር ጳውሎስ ተካልኝ ናቸው።

ምዕራባዊያን ልዩነቶችን አክብሮትና ዕውቅና ሰጥተው  ሀገራዊ አንድነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚንቀሳቀሰው ከአሁኑ መንግስት ጋር መስማማት ትተው ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር  መተባባራቸው  ተገቢነት እንደሌለው ነው ያመለከቱት።

አሸባሪው ለሀገርና ለዜጎች የሚጠቅም ዓላማ ይኖረዋል ብሎ ካሰቡም  በራሱ ስህተት ነው ሲሉም አክለዋል።

የሀገሪቱ ሕዝብ ይወክለኛል ብሎ ለመረጠውና  ድጋፉን በተለያየ መልክ እየገለፀለት ባለው የራሱ መንግስት እንጂ በውጭ ኃይሎች የሚወሰንለት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

አሜሪካን ጨምሮ ሌሎችም የምዕራባዊያን ሀገራት በሰብዓዊ መብት ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱ ያሉት ጫና ምክንያቱ ለነሱ  ተላላኪ መንግስት እንዲኖር መሆኑን ነው ምሁራኑ የገለጹት።

የአፍሪካ ቀንድን ለመቀራመት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ጭምር ነው፤  ይህንን ጫና ለመቋቋም የኢትዮጵያን እውነት ለሌላው ዓለም ለማስረጽ መረባረብ እንደሚኖርብን ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም