ምርት ገበያው በአራት ወራት የ4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ምርት አገበያይቷል - ኢዜአ አማርኛ
ምርት ገበያው በአራት ወራት የ4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ምርት አገበያይቷል
ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት አራት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የግብርና ምርት ማገበያየቱን ገለጸ።
ምርት ገበያው በተጠቀሰው ጊዜ 51 ሺህ 640 ሜትሪክ ቶን ቡና፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ አረንጓዴ ማሾ፣ የተለያዩ የቦሎቄ ዝርያዎች እና አምስት ቶን የርግብ አተር አገበያይቷል።
የምርቶቹ መጠን 17 ሺህ 690 ቶን ቡና፣ 15 ሺህ 445 ቶን ሰሊጥ፣ 3 ሺህ 24 ቶን ነጭ ቦሎቄ፣ 4 ሺህ 731 ቶን አኩሪ አተር፣ 3 ሺህ 368 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 1 ሺህ 904 ቶን ዥንጉርጉር ቦሎቄ፣ 215 ቶን ቀይ ቦሎቄና አምስት ቶን የርግብ አተር መሆናቸውን ምርት ገበያው ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመላክቷል።
አረንጓዴ ማሾ በዓለም ገበያ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ ምርት ገበያው የሚገበያይበት ዋጋም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
በሐምሌ 2013 ዓ.ም 7 ሺህ 235 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል የአረንጓዴ ማሾ አማካይ የግብይት ዋጋ ሲሆን በጥቅምት ወር ወደ 7 ሺህ 841 ብር አድጓል።
ይህ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን መግለጫው ጠቁሟል።
የገበያው መጨመር አርሶ አደሮችና አቅራቢዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፤ በመጪው ወር ጥራት ያለው አረንጓዴ ማሾ በከፍተኛ መጠን ለገበያ እንደሚቀርብም ይጠበቃል።
በተመሳሳይ የቀይ ቦሎቄ ግብይት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን ከ50 በመቶ በላይ፤ በዋጋ ደግሞ በእጥፍ አድጓል።
ይህ ለውጥ ሊመጣ የቻለው በግብይቱ ላይ ይስተዋል የነበረውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በመግታትና የገንዛቤ ማስጨበጫ በመሰራቱ ነው ብሏል ምርት ገበያው።
የደንበኞችን ፍላጎት መሰረተ በማድረግ የአሰራር ማሻሻያ መደረጉም ውጤት ማስገኘቱ ተጠቁሟል።
ጥቁር አዝሙድ፣ ድንብላል፣ አብሽና ቁንዶ በርበሬ፤ እንዲሁም ጓያ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ የተካተቱ ሲሆን ከተያዘው ምርት ዘመን አንስቶ ግብይት ይካሄድባቸዋል።