የዲፕሎማሲ ማዕከል ማቋቋሚያ ፕሮግራም በሀዋሳ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲፕሎማሲ ማዕከል ማቋቋሚያ ፕሮግራም በሀዋሳ እየተካሄደ ነው
ሀዋሳ ፤ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ ማዕከል ማቋቋሚያ ፕሮግራም እየተካሄደ ነው።
"ሁሉም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ እንደ አንድ ዜጋ ለሀገሩ ዲፕሎማት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው ፕሮግራም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዩኒቨርሲቲው በዲፕሎማሲ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብር ማህበረሰብን በማነቃቃት ረገድ የወሰደው ተነሳሽነት የሚያስደስት ነው ብለዋል ።
ኢትዮጵያ በለውጡ ሂደት እያስመዘገበች ያለው ውጤት በተለይም ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናከር ያሳየችው አቅም ዕድገቷን በማይሹት ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
"በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ችግርም የምዕራባውያንና የሌሎችንም ረጅም እጅ አይተናል፤ እነዚህን ፈተናዎች በማለፍ የምንፈልገውን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ ዲፕሎማት መሆን አለበት" ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ምሁራን ፣ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ባሉበት ፕሮግራም የማዕከሉ መቋቋም አስፈላጊነት ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
የዲፕሎማሲ ማዕከሉም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንደሚከፈት ተመልክቷል።