ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራውን መስዋትነት ከፍለን እናከሸፈዋለን

ባህር ዳር፤ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በእብሪት ተነሳስቶ ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራውን ከሠራዊቱ ጋር በመሆን መስዋትነት ከፍለን እናከሽፈዋለን ይላሉ እህታማማችና ወንድማማች ተመራቂ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት ።
እህታማማችና ወንድማማቾቹ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ በዘጠነኛ ዙር ካስመረቃቸው የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት መካከል ይገኙበታል።

አሸባሪው የህውሃት ቡድን ህዝብን ለማዋረድና  ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ለማፍረስ ከውጭ ሃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ ይገኛል ብላለች  ከእህታማማቾች አንዷ ኮንስታብል እመቤት ጌቴ።

 ''እኛ የጀግኖች አባቶቻችን ልጆች በህይወት ቁመን እያለን  ቡድኑ በሴራ ፖለቲካ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ  እናከሽፈዋለን '' ስትል ለኢዜአ ተናግራለች።

በውትድርና ሙያ ተሰማርቶ የሃገርን ዳር ድንበር ማስጠበቅ የልጅነት ህልሟ እንደነበር ጠቅሳለች።

"ካሁን ቀደምም ታናሽ ወንድሜ የክልሉ ልዩ ሃይል አባል ሆኖ ወደ ግዳጅ ማቅናቱ ደግሞ ይበልጥ የልጅነት ህልሜን ለማሳካት አነሳስቶኛል" ብላለች።

ለዚህም የክተት ጥሪውን በመቀበል የእናቷ ልጅ ከሆነችው ከኮንስታብል ዘውዲቱ ሁኔ ጋር ሆነው ወደ ልዩ ሃይል ማሰልጠኛ ጣቢያ በደስታ መግባታቸውን አመልክታለች።

አሸባሪው  በወረራ  በያዛቸው አካባቢዎች ንፁሃንን ከመግደል፣ ንብረት ከመዝረፍና ከማውደም በላይ ሴት እህቶቻችን በመድፈር በቁም እያዋረደ  ነው ብላለች።

''የመጣብንን ወራሪና የሃገር ጠላት በአንድነት መደምሰስ አለብን፤  ሃገር ከሌለች እኛም መኖር ስለማንችል በህብረት መፋለም ይገባናል ነው ያለችው ኮንስታብል እመቤት።
 ''እኔ እና እህቴ ይህ የሽብር ቡድኑ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን በደልና ሃገርን ለመበተን የያዘውን ሴራ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን መስዋዕትነት ከፍለን ለማክሸፍ ተዘጋጅተናል'' ብላለች።

 ኮንስታብል ዘውዲቱም የእህቷን ሀሳብ ትጋራለች።

ከወንድማማቾቹ መካከል ኮንስታብል በላይ እንዳወቀ በበኩሉ፤አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሴቶች፣ ህፃናትና አረጋውያን ሲንገላታ፤ ህዝብ ሲያዋረድና  ሃገር ስትደፈር ቁሞ እንደማየት የሞት ሞት የለም ይላል።

በቡድኑ ወገን በሰላም ከሚኖርበት ቀየ ሲፈናቃል፣ ለሞትና ለመከራ ሲዳርግ አይቶ በመቆጣት  ወደ ልዩ ሃይል ለመቀላቀል ምክንያት እንደሆነው ተናግሯል።

"በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ከታናሽ ወንድሜ ጋር ጁንታውን ለመፋለም በመዘጋጀቴ ደስተኛ ነኝ" ብሏል።

በቀጣይም ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን በገባበት ገብቶ በቆራጥነት የሚከፈለውን መስዕዋትነት በመክፈል የጥፋት ሴራውን ለማክሸፍ  ቁርጠኛ መሆኑን ነው  ኮንስታብል በላይ የገለጸው።

ታናሽ ወንድሙ ኮንስታብል ፈጠነ እንዳወቀ እንዳለው፤ ይህ የአሸባሪው ቡድን ለማንም ምህረት የሌለውና ጨካኝ በመሆኑ ተረባርቦ ባለበት ማጥፋት ይገባል።

የቡድኑን  ሰይጣናዊ ሃሳቡና ተግባር ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር  ታግሎ ለማምከን  መዘጋጀቱን ተናግሯል።

''እኛ  የሃገር መደፈር እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው የጀግኖች አባቶቻችን ልጆች ነን'' ያለው ኮንስታብል ፈጠነ፤ በማሰልጠኛ ጣቢያው ያገኘውን  የውጊያ ክህሎት ተጠቅሞ በጀግንነት በመዋደቅ ህዝቡንና ሃገሩን ከአሸባሪው ቡድን  ጥፋት ለመታደግ ቆርጦ መነሳቱን አስታውቋል።

ለሃገርን ሰላም ፀር የሆነው አሸባሪው ህወሃትን  ለማስወገድ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክቷል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ በዘጠነኛ ዙር ያሰለጠናቸው የልዩ ሃይል አባላት የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፍአለን ጨምሮ ሌሎችም የፌደራልና ክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት  መገኘታቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም