ኦቢኤን ለመከላከያ ሰራዊት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኦቢኤን ለመከላከያ ሰራዊት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ህዳር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኦቢኤን በአፋር ግንባር ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የእርድ እንስሳትና የምግብ ድጋፍ አደረገ።
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ድጋፉን ያደረገው አሸባሪው ህወሃት ውጊያ በከፈተበት የአፋር ግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት እና በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው።
በዚህም ለተፈናቃዮች 400 ኩንታል ስንዴ ሲለግስ ለሰራዊቱ ደግሞ 15 ሰንጋዎችን አበርክቷል።
በስፍራው በመገኘት ድጋፉን ያስረከቡት የኦቢኤን ዋና ዳይሬክተር ዝናቡ አስራት፤ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ከማድረስ ባለፈ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኦቢኤን የሕልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ በሁሉም ግምባሮች ጋዜጠኞችን በማሰማራት ለሕዝቡ ትክክለኛ ዘገባ ሲያደርስ ቆይቷል፤ አሁንም ማድረሱን ቀጥሏል ብለዋል።
አሁንም የኦቢኤን ሰራተኞች ከደሞዛቸው ቀንሰው ለሰራዊቱና በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የእርድ እንስሳትና የምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ኦቢኤን ከዚህ በፊትም በተለያዩ አካባቢዎች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ሲደግፍ መቆየቱንና ለሰራዊቱም ሰራተኞቹ የአንድ ወር ደሞዝ መለገሳቸውን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ተቋሙ ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝቡ እያደረሰ፣ ድጋፍ ማድረግ ባለበት ጊዜም ድጋፍ ማድረጉን የሚቀጥል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
የመከለከያ ሰራዊትን ወክለው ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ እዝ ሎጂስቲክስ፣ ቀለብና ንብረት መምሪያ ኃላፊ ሻለቃ ጌታቸው አስማረ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደጀንነቱንና እያስመሰከረ ቀጥሏል ብለዋል።
የአገር ህልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚችለው ሁሉ ሰራዊቱን እያገዘ እያበረታታ እና አጋርነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም የአገር መከለከያ ሰራዊት በቆራጥነት መስዋዕትነት እየከፈለ የአገር ሉዓላዊነትን እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በጋራ እያደረጉት ያለው አገር የማስከበር ዘመቻ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ይጠናቀቃል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአፋር ክልል ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ከሎኢታ፤ ኦቢኤን ላደረገው ድጋፍ በክልሉ ሕዝብና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።