በደብረማርቆስ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን በማዘዋወር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

217

ደብረ ማርቆስ ፤ ህዳር 9/2014 በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ37 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የባለ 200 ብር ኖቶችን በማዘዋወር ወንጀል የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
 በከተማ አስተዳደሩ የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ  ጽፈት ቤት የሙስና ወንጀሎች ክፍል ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ጌታቸው ባዘዘው እንደገለጹት ተጠርጣሪቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በኅብረተሰቡ ጥቆማ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ነው።

በዚህም አንዱ ተጠርጣሪ በከተማው ቀበሌ ስምንት የሞባይል ካርዶችን በመግዛት ላይ እንዳለ ከ600 በላይ ሃሰተኛ ብር ጋር መያዙን ተናግረዋል።

በግለሰቡ ላይ በተካሄደው ምርመራም ሁለት ጓደኞቹ በተመሳሳይ  ተግባር መሰማራታቸውን በጠቆመው መሰረት በአንደኛ ተጠርጣሪ ላይ 200  እና በሌላኛው ደግሞ  36ሺህ 400 ሃሰተኛ የብር ኖቶች ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል  ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ላደረገው ትብብር ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ኢንስፔክተር ጌታቸው፤  በቀጣይም ተመሳሳይ ድርጊት ሲያጋጥም  ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።


የሀሰተኛ ብር  ኖቶች ዝውውር እየተስፋፋ በመሆኑ ህብረተሰቡ በግብይት ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም