አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳዊ ውድመት አድርሷል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳዊ ውድመት አድርሷል
ህዳር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳዊ ውድመት አድርሷል፡፡
በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት መደገፍና የወደሙ ተቋማትን ማቋቋም ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የአፋር ተወላጆች በወቅታዊ አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
በምክክር መድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሀራ ሁመድ አሊ ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ተወላጆች ተሳትፈዋል።
በግንባር አኩሪ ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአፋር ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ እንዲሁም በአሸባሪው ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ደግሞ የምክክሩ ዋነኛ ዓላማ መሆኑ ተጠቅሷል።
በመድረኩ አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል በአፋር ክልል በገባባቸው አካባቢዎች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳዊ ውድመት ማድረሱ ተገልጿል።
የሽብር ቡድኑ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመፈጸም በርካታ ንጹኃንን ለህልፈት የዳረገ ሲሆን፤ ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ወገኖች ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው በማፈናቀል ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት እንዲጋለጡ ማድረጉ ተነስቷል።
በንጹኃን ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት የሽብር ቡድኑ አካላት ኢ-ሰብዓዊነት የተላበሱ የጥፋት ሃይሎች መሆናቸው ተመላክቷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሀራ ሁመድ አሊ፤ "አሸባሪው ህወሓት ወራሪ በፈጸመባቸው የአፋር ክልል አካባቢዎች እንስሳትን መግደል ጨምሮ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋማትን ከጥቅም ውጭ በማድረግ ማህበረሰቡን ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ዳርጓል" ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በቋሚነት ለመደገፍም የአፋር ተወላጆችንና ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ከአፋር ልማት ማህበር ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት ወራሪም በአፋር ክልል በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በአፋር አናብስቶችና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ድባቅ እየተመታ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ጊዜያት የተሟላ ሰላም መምጣቱ አይቀርምና የሽብር ቡድኑ ጉዳት ያደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ በመገንባት ማህበረሰቡ በየአካባቢው ሲመለስ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ኃላፊ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፤ ግንባር ላይ እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት ደጀን ለመሆንና በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው ለሰብዓዊ ቀውስ የተዳረጉ ወገኖችን ለመደገፍ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለድጋፉ ስኬታማነት በመንግሥት ተቋማት ያሉ አመራሮችን፣ በክልሉ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶችንና ሌሎች ኢትዮጵዊያንን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖችና መከላከያ ሠራዊት የሚችሉትን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ድጋፉን የሚመሩ ኮሚቴዎችን በማዋቀርም የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
መላው ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል አማካኝነት ለከፋ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ሰለባ ለሆኑ ንጹኃን ወገኖች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።
በመድረኩ በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ለተጋለጡ ዜጎች፣ ውድመት ለደረሰባቸው ተቋማት እና በግንባሩ ፍልሚያ እያደረገ ለሚገኘው ሠራዊት ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።