ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ምርቶች ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ይገባል

ህዳር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ማዕቀፍ ማስወጣቱን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ ገበያ በማስፋት በኩል ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 39 የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ የሚያስገቡበትን አጎዋ የንግድ ማዕቀፍ ሥራ ላይ አውላለች።

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2000 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለውን የንግድ ማዕቀፍ እስከ 2025 ድረስ ለማቆየት ውጥን ተይዟል።

ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ባልተገባ መልኩ ከማዕቀፉ ለማስወጣት የሚያስችለውን ውሳኔ በቅርቡ አሳልፏል።  

በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ማዕቀፍ ማስወጣቱን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ ገበያ በማስፋት በኩል ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር መንግሥቱ ከተማ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር መንግሥቱ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከማዕቀፉ እንድትወጣ የአሜሪካ መንግስት መወሰኑን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።        

ኢትዮጵያ የአጎዋን እድሉ በመጠቀም የጨርቃጨርቅና የቆዳ ውጤቶችን ወደ አሜሪካ በመላክ ተጠቃሚ እንደነበረች አስታውሰው አሁን ላይ በመቅረቱ አማራጭ ገበያዎችን ማፈላለግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ነው ያሉት።

ከዚህ በፊት እንደ ሚደረገው የተወሰኑ ምርቶችን ብቻ ወደ ውጭ በመላክ ችግሩን መፍታት እንደማይቻል ጠቁመው ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት ማደግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

አገሪቷ ሊገጥማት የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መምረጥ ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት ፕሮፌሰር መንግሥቱ።    

አገሪቷ ምን ማስገባት አለባት? የሚለውን በአግባቡ ማጤን የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ለምርት ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ላይ ማተኮር እንዲሁም ከውጭ የሚገቡትን በአገር ውስጥ የመተካት ጥረቱን ማጠናከር ከመፍትሄዎች መካከል መሆኑን አመላክተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በቶሎ በማጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ጎረቤት አገራት በመላክ የውጭ ግኝትን ማሳደግና በአገሪቷ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሃብት ብክነት መቀነስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።          

በተለይም በግብርናው ዘርፍ ከ26 እስከ 30 በመቶ የምርት ብክነት መኖሩን የተናገሩት ፕሮፌሰር መንግስት ብክነቱን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም