አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች፣ አለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታትና ግለሰቦች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የፖሮፖጋንዳ ጦርነት አካል መሆናቸውን ታዝቤያለሁ - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች፣ አለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታትና ግለሰቦች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የፖሮፖጋንዳ ጦርነት አካል መሆናቸውን ታዝቤያለሁ
ህዳር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) “አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች፣ አለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታትና ግለሰቦች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የፖሮፖጋንዳ ጦርነት አካል መሆናቸውን ታዝቤያለሁ” ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትገለጸ።
የጋራ ምክር ቤቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤትና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል መሆኗን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት እንዲፈጠር ለረጅም ጊዜ ሙከራዎችን ስታደርግ እንደነበርና ለዚህም በርካታ የህይወት መስዋትነት መከፈሉን አስታውሷል፡፡
አሁን ለተፈጠረው ጦርነት መንስኤው አሻባሪው የህወኃት ቡድን መሆኑን ጠቅሶ፤ “ከሃያ ዓመታት በላይ ተቀማጭነቱን ትግራይ ላይ ባደረገው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው የክህደቱ ጥግ ማሳያ እንደሆነ አለም ሊገነዘብ ይገባል” ብሏል፡፡
በአሸባሪው ህወሃት የተጀመረው ጦርነት እየሰፋ በመምጣቱና በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች ህዝቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ማስከተሉንና ለዚህም ምክንያቱ የአሸባሪው ህወኃት የሀገር አፍራሽነት ጦረኝነት እንደሆነ መግለጫው አውስቷል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ “አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች፣ አለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታትና ግለሰቦች የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማዛባት እየተበተነች አስመስለው የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የፖሮፖጋንዳ ጦርነት አካል መሆናቸውን ታዝቤያለሁ” ብሏል፡፡
ከህጋዊ መንግስት ውጭ የትኛውንም የአሻጉሊት መንግስት በህዝብ ላይ የመጫን ሀሳብ የኢትዮጵያ ህዝብ በፍጹም እንደማይቀበልና የጋራ ምክር ቤቱም በጽኑ የሚያወግዘው መሆኑን አሳስቧል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች እና በሀገራችን ወቅታዊ ችግር ምክንያት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ህዝቡ ተደራጅቶ ሀገሩን ከውስጥና ከውጭ ጠላት እንዲጠብቅ አሳስቧል።
በተለያዩ ቦታዎች አሸባሪው ሀይል ከመኖሪያ ቄዬአያቸ ያፈናቀላቸውን ንጹሀን ዜጎች መንግስትና ህብረተሰቡ በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጠቀሜታ አድንቆ፣ አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግ ንጹሃንን እንዳይጎዳ በጥንቃቄ እንዲፈጸምና መንግስት የጀመረውን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቁን የጋራ ምክር ቤቱ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።