የህወሓት ወራሪ ሀይልን በመደምሰስ ወገኖቻችንን ከመከራ ለማውጣት ተዘጋጅተናል--ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ወራሪ ሀይልን በመደምሰስ ወገኖቻችንን ከመከራ ለማውጣት ተዘጋጅተናል--ነዋሪዎች
ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 9/2014 ''የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ሀይልን በመደምሰስ ንጽሀን ወገኖቻችንን ከሚፈፀምባቸው ግፍና መከራ ነፃ ለማውጣት ተዘጋጅተናል'' ሲሉ የምዕራብ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ።
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙበት የህዝብ ንቅናቄ ኮንፍረንስ በዞኑ ቡሬ ከተማ ተካሂዳል።
ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የወንበርማ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጠብቀው ዳኘ እንዳሉት፣ በሀገርና በህዝብ ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠውን ህወሓት ለመደምሰስ ሁሉም ያለውን ይዞ መዝመት ይኖርበታል።
"አባቶቻችን በደምና አጥንታቸው ከውጭ ወራሪ ነፃ ያወጧትን ሀገር አሸባሪው ህወሀት በአማራና በአፋር ክልል ወረራ በመፈፀም እንዲያፈርሳት አንፈቅድም" ያሉት አቶ ጠብቀው፣ ወራሪው ሀይል በወገኖች ላይ ሰይጣናዊ ድርጊት እየፈፀመ ነው" ሲሉል ተናግረዋል ።
ወራሪው ንፁሀንን በመግደልና ሴቶችን በመድፈር አማራን አንገት ለማስደፋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ "እድሜየ ቢገፋም የአሸባሪውን ወራሪ ሀይል ከገባበት ገብቸ ለመደምሰስ ተዘጋጅቻለሁ" ሲሉ በጽናት ገልጸዋል።
የሰሜን ሜጫ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደባሱ ገዳሙ በበኩላቸው ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር መንገድ የመሩ ባንዳዎችን በማስታወስ "ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ" አሸባሪው ህወሓት በአሁኑ ወቅት ሀገርን በመካድ በጥፋት ተግባር ውስጥ መሰማራቱን አመልከተዋል።
የአሁኑ ትውልድም የቀደሙ አባቶቻችንን ወኔ በማንሳት ብቻ ሳንወሰን በተግባር የጀግኖች አባቶችን ታሪክ መድገም እንደሚገባው አሳስበዋል።
ቀደም ሲል ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸውንና የውጊያ ልምድ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ደባሱ፣ አሁንም በባንዳነት ተግባር የተሰማራውን ጠላት ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
''ሽብርተኛው ህወሀት እየተዋጋን ያለው በጦር መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ትልቁን የስነ-ልቦና ጦርነት በመንዛት ጭምር ነው'' ያሉት ደግሞ የቡሬ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ደመቀች በየነ ናቸው።
"ወራሪ ሀይሎች ያበላቸውንና ያበለፀጋቸውን ህዝብ እየነከሱና እየወጉ በመሆኑ ህዝቡ በራሱ ላይ እስኪደርስ ሳይጠብቅ የአሸባሪውን ግብአተ መሬት ማፋጠን አለበት " ሲሉ አመልክተዋል።
"አሸባሪው ህወሀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በርካታ የአማራ ክልል የወረረበት ጊዜ ላይ እንገኛለን" ያሉት ደግሞ ባለሃብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ናቸው።
ባለሃብቶች የሀገርና የህዝብ ጠላት የሆነውን አሸባሪውን ሀይል ለመደምሰስ በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት ያልተቋረጠ የሎጀስቲክ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
"ሁላችንም በአንድነት በመነሳትና በመዝመት ወራሪውንና ዘራፊውን ጠላት ለመደምሰስ ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል" ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ በበኩላቸው "በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩንም ቅድሚያ እየነደደ ያለውን ቤታችንን ለማጥፋት በጋራ እንነሳ" ብለዋል።
"በቅድሚያ ሀገራችንንና ህዝባችንን ለማዳን በጋራ ወደግንባር ዘምተን ጠላትን ድል የምናደርግበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ሲሉም አክለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋአለ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሀት አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን አፍርሰን ታላቋን ትግራይ ዕውን እናደርጋለን በሚል ቅዠት ከታሪካዊ የውጭ ጠላቶቻችን ጋር ተባብሮ እየወጋን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"ህወሀት ባለፉት 40 ዓመታት የአማራን ህዝብ የሌላው ብሔር ጠላት እንደሆነና እንዲጠላ፣ ባህሉ እንዲጠፋ፣ እንዲሸማቀቅና አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር በርካታ ሥራዎች ሲሰራ ነበር" ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።
ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ጠላቴ ያለውን ጥፍር ሲነቅልና ብልት ሲያኮላሽ የኖረው አልበቃ ብሎት ዛሬም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘውን ሴራ ለማሳካት ወረራ በመፈጸም በንጽሀን ህዝብና ሀገር ላይ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል ።
"አሁን ላይ አሸባሪውን ወራሪ ሀይል እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ በአንድነት ወደ ግንባር የምነዘምትበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ሲሉም አክለዋል።
ህዝቡ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ ግንባር ለሚገኘው ኃይል ያልተቋረጠ የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዶክተር ይልቃል አሳስበዋል።