ተቋማቱ የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግርን በመቀነስ ረገድ በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግርን በመቀነስ ረገድ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
ህዳር 9/2014/ኢዜአ/ የጤና ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች የመላመድ ችግርን በመቀነስ ረገድ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ።
የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ባለሙያ ትእዛዝ የመጠቀም ልምድ መበራከት የመድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግር እንዲስፋፋ ማድረጉም ተገልጿል።
ስምምነቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እና የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ተቋማቱ በግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች አጠቃቀምና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በጋራ የሚሰሩ ይሆናል፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ የሚከበረውን ''ዓለምአቀፍ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት'' አስመልክቶ መሆኑም ተገልጿል።
የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት በሰውና በእንስሳት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
መድሃኒቶቹ በዋናነት ሰውን፣ እንስሳትንና አጽዋትን ለማከም አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሲሆን፤ አሁን አሁን ከባለሙያ ትእዛዝ ውጪ መድሃኒቶቹን የመጠቀም ልምድ እየጨመረ መጥቷል፡፡
ይህም የፀረ-ተህዋሲያን በጀርሞች መላመድ ችግር እንዲስፋፋ አድርጓል።
በዚህም ህሙማን በወሰዱት መድኃኒት በቀላሉ መዳን ሲገባቸው፤ መድኃኒቱ በመላመዱ ሳቢያ ለተባባሰ የጤና ችግር እንዲጋለጡ ያደርጋል።
ይህ ችግር በዓለም ከተመዘገቡ አሥር አሳሳቢ የጤና ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት አገራት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ የዓለም የጤና ድርጅት አሳስቧል።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ እያደጉ ባሉ አገራት ደግሞ ችግሩ ይበልጥ የከፋ መምጣቱም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ጤና ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴርና የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ችግሩን በመቀነስ ረገድ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ የፀረ-ተህዋሲያን በጀርሞች መላመድ ችግርን ለመቀነስ በዓለምአቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከእነዚሁም ተግባራት መካከል የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች አጠቃቀም ማሻሻልና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንፌክሽንን መከላከል፣ በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩ ጥናቶችን መተግበር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ዋነኞቹ ተግባራት እንደሆኑ ነው የገለጹት።
ስምምነቱ ችግሩን ከመቀነስ አኳያ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው የቲቢ፣ የገንዲ በሽታ፣ የላሞች ግት በሽታ ኤች.አይ.ቪ እና የወባ መድኃኒቶች በጀርሞች እየተላመዱ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
ችግሩ በሰውና በእንስሳ ላይ ከሚያደርሰው የጤና ተጽእኖ ባሻገር ኢኮኖሚው ላይም ጫና እንደሚያሳድር ጠቁመዋል፡፡
ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2015 በእንሰሳት ሃብት ላይ 11 በመቶ የምርት መቀነስ ሊያጋጥም እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አንስተዋል።
የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድ ችግርን መቀነስ የአንድ ተቋም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ናቸው
ችግሩ በተለይም በእጽዋት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እያየለ መምጣቱን ገልጸው፤ ስምምነቱ ችግሩን በአገር ደረጃ ለመቀነስና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በኢትዮጵያ ከህዳር ዘጠኝ እስከ 15/2014 ዓ.ም በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሮች፣ በውይይት እና የጤና ተቋማት አሰራራቸውን በመጎብኘት የሚከበር ይሆናል።
ሳምንቱ ''ግንዛቤን በመፍጠር የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን እንከላከል'' በሚል መሪ ቃል እንደሚከበርም ተነግሯል።
የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን ተከትሎ በዓለም በየዓመቱ ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።