ቀጥታ፡

ወጣቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የቅድመ አያቶቹን ታሪክ እየደገመ ነው

ባህር ዳር፤ ህዳር 9 /2014 (ኢዜአ)፡ ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እያደረገ ያለው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የቅድመ አያቶቹን ታሪክ እየደገመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው የአማራ ክልል አረጋዊያን ማህበር አባል
የአማራ ክልል አረጋዊያን ማህበር  አባል አቶ ስራው ይሁን ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ወጣቱ ስለሀገሩና ስለ ወገኑ ፍቅር እንዳይኖረውና እራስ ወዳድ እንዲሆን ሲሰራ ቆይቷል።

ወጣቱ የሀገሩን ታሪክ በተሳሳተ መልኩ እንዲረዳ ከማድረግ ባለፈ የሀሰት ትርክቶችን በማራመድ ትውልዱ እርስ በርስ እንዲቃቃርና ሀገር ጠል እንዲሆን ሰርቷል።

ይሁን እንጂ ወጣቱ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሲወድቅ የጎንዮሸ ቅራኔዎች ቦታ እንደማይኖራቸው በመረዳት እንደ ቀድመ አያቶቹ ሁሉ በጋራ ሆኖ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሽብር ቡድኑን በጀግንነት እየተፋለመው ይገኛል።

''ዘመኑ ዳግማዊ የዓድዋ ጥሪ ይመስላል'' ያሉት አቶ ስራው፤ የሀገርን ጥሪ መነሻ በማድረግ ከ100 ዓመት በፊት ዳግማዊ ዓፄ ሚኒልክ ያስተላለፉትን ሀገር የመታደግ ጥሪ ወጣቱ ትውልድ በዚህ ዘመን በተግባር አሳይቷል።

ዓፄ ሚኒልክ የጣሊያንን ወረራ ለመመከት ለመላ ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ሲያስተላልፉ በዘመኑ በተለያየ መንገድ ያኮረፉ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ነገር ግን ኩርፊያውን እና ልዩነቱን  ወደ ጎን ትተው  የመሪያቸውን ጥሪ ተቀብለው ጠላትን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ወረራው አክሽፈዋል።

ዛሬም ትውልዱ የአሸባሪው ህወሓትን የሀሰት ትርክቶችና መቃቃሮች ወደ ጎን በመተው በሀገር ላይ የተደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመመከት በጋራ መቆም መቻሉን አስረድተዋል።

ወጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድነቱን አዳብሮ ለሀገሩ ዘብ መቆሙን ያመለከቱት አቶ ስራው፤ የህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በሴራ የማይደበዝዝ የሀገር ፍቅር እንዳላቸው በግልጽ ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለያዩ አደረጃጀቶች ተሰልፎ እያደረገ ያለው ሀገርን  የማዳን እንቅስቃሴ እንደቀደምት አባቶቹ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ብለዋል።

ሀገር የማዳንና የማስጠበቅ ተጋድሎውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቱ የሀገሩን ህልውና ለማስጠበቅ በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተሳተፈና መስዋትነት እየከፈለ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ፌዴሬረሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ዘላለም ታከለ ነው።

ፕሬዚዳንቱ እንዳለው ወጣቱ በተለያዩ አደረጃጀቶች ታቅፎ በፍልሚያው አውደ ግንባር ተሰልፎ መስዕዋትነት እየከፈለ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተዋደቀ ነው።

እንዲሁም በግንባር ለተሰለፈው የፀጥታ ኃይል የኋላ ደጀን ሆኖ ስንቅ በማቀበል ሥምር ሌሎች ሁለንተናዊ ድጋፎችን በማድረግ አኩሪ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።

የሕልውና ትግሉ በድል ከተጠናቀቀ በኋላም የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚከናወኑ ተግባራት የወጣቱ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንሚቀጥልም አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም