ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለመከላካያ ሠራዊትና ለተፈናቃዮች 106 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደርጓል

ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለመከላካያ ሠራዊትና ለተፈናቃዮች 106 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ።
የባንኩ አመራሮችና ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

በመርኃ ግብሩ የተገኙት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዘዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ባንኩ  ለህልውና ዘመቻ የሚውል የተለያየ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

የህሕልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ ለህልውና ዘመቻውና ለተፈናቃዮች 106 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የባንኩ ሠራተኞች በራሳቸው ፈቃድ የአንድ ወር ደሞዛቸውን (27 ሚሊዮን ብር) ለአገር መከላከያ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

የክተት ጥሪውን ተከትሎ የሕልውና ትግሉን የተቀላቀሉ የባንኩ ሠራተኞች መኖራቸውንም  ገልጸዋል።

በቀጣይም ባንኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው ዘመቻው የኔነት ስሜትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ በተካሄደው የደም ልገሳ መርኃ ግብር 130 የባንኩ አመራሮችና ሠራተኞች ደም መስጠታቸው ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ኦፊሰር አብርሃም ከተማ ደም ከሰጡት የባንኩ ሰራተኞች መካከል ነው።

የሰጠውም ደም ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚውል በመሆኑ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ገልጿል።

በየተቋማቱ ለህልውና ዘመቻው የደም ልገሳ መርኃ ግብሮች መከናወናቸው ሰዎች የደም መስጠት ባህልን እንዲያዳብሩ ያግዛል ብሏል።

በባንኩ የደንበኞች መረጃ አገልግሎት ባለሙያ የሆነችው ገነት ቦጋለም  የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብላለች።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም