በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በአሸባሪው የሸኔ አባላት ላይ የተቀናጀ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በአሸባሪው የሸኔ አባላት ላይ የተቀናጀ እርምጃ ተወሰደ

ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሚንቀሳቀሱ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ላይ ሰሞኑን የተቀናጀ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ አባላት ጋር በመቀናጀት ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ባካሄደው የማጥቃት ዘመቻ በርካታ የሸኔ አባላት መደምሰሳቸው ተገልጿል።
አስር ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፀው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፤ አሸባሪዎቹ በወቅቱ ሲጠቀሙበት የነበረ በርካታ ገንዘብም ተይዟል፡፡
የአሸባሪው ህወሃት ተላላኪ የሆነው አሸባሪው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጮመን ወረዳ በፈጫሰ፣ አየለ፣ ችንቦና በመሳሰሉት ቀበሌዎች የንፁሃን ዜጎችን ህይወት፣ የህዝብ ንብረቶችን በማውደም፣ በማጥፋትና መንገድ በመዝጋት ህብረተሰቡን ለእንግልትና ስቃይ መዳረጉ ታውቋል፡፡
ህብረተሰቡ ለፀጥታ ሀይሉ ባደረሰው ጥቆማ የአሸባሪ ቡድኑ አረመኔያዊ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ የተሸሸገበት ሥፍራ በመድረስ በፀጥታ ሀይሉ የተቀናጀ እርምጃ እንደተወሰደበት ተገልጿል፡፡
በጮመን ወረዳ ገበቴ ከተማ አስር የአሸባሪው ሸኔ ተባባሪ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡