አሸባሪው ህወሓትን በመደምሰስ የሀገርን ህልውና ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓትን በመደምሰስ የሀገርን ህልውና ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን
አርባ ምንጭ፤ ህዳር 09/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓትን በመደምሰስ የሀገርን ህልውና ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን በጋሞ ዞን የሚገኙ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ገለጹ፡፡
የሰራዊት አባላቱ በመንግስት የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ አስታውቀዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ አስር አለቃ መኮንን ገብረእየሱስ መንግስት ለቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ልጆቼን ማሳደግ የምችለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው" ያሉት አስር አለቃ መኮንን፤ ''ለሀገሬ ብሰዋ እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቼን እንደሚያሳድግ እርግጠኛ ነኝ'' ብለዋል።
የሀገርን ህልውና ለማስከበር ያለው ብቸኛ አማራጭ አሸባሪዎችን ከኢትዮጵያ ምድር ማጽዳት መሆኑን አመልክተዋል።
"በህወሓት የግፍ አገዛዝ ላለፉት 27 ዓመታት የተንገላታው የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በኋላ ለአሸባሪው እሾህ ይሆናል እንጂ ጫንቃው ላይ እንዲወጣ አይፈቅድም" ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባልነት ለሰባት ዓመታት ሀገርና ህዝብ ማገልገላቸውን የተናገሩት ሌላው ምክትል አስር አለቃ መስፍን መንግስቱ በበኩላቸው ''የሀገሬ ሉዓላዊነት እስኪረጋገጥ ድረስ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት ሀገርና ህዝብን ሲያገለግል በነበረው መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ግፍ ለትውልድ የሚቀመጥ ጥቁር አሻራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገርና ህዝብ ዘላቂ ሰላም እስኪረጋገጥ ህብረተሰቡ አንድነቱን በማጠናከር ለመከላከያ ሠራዊቱ እያደረገ ያለውን ደጀንነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል ወታደር ትንሳኤ አገኘው በበኩላቸው የአሸባሪው ህወሓት አረመኔያዊ ተግባር በሰው ልጅ አዕምሮ ሊታሰብ የማይችል መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገርን ማገልገል ትልቅ ክብርና ሃላፊነት መሆኑን የገለጹት የመከላከያ ሠራዊት አባሉ መንግስት ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላም ሊኖር የሚችለው አሸባሪዎች ከኢትዮጵያ ምድር ሲጸዱ በመሆኑ ወራሪ ሀይሉን ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።