ቀጥታ፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የደህንነታችን ዋስትና በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅብንን እየተወጣን ነው

አርባ ምንጭ ፤ ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና ደህንነታችንን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ የበኩላችንን እየተወጣን ነው ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አዋጁ ከወጣ ወዲህ  በዞኑ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታውቋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታዬ መኩሪያ፤  የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተግባር በምንም ተአምር የምንታገሰው አይደለም ብለዋል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱን  ደህንነት የሚያስጠብቅ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ከአስፈጻሚው አካል ጋር በመሆን የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከኬንያ እስከ አዲስ አበባ በርካታ አካላት አርባ ምንጭ ከተማን አቋርጠው የሚያልፉ በመሆናቸው ጠበቅ ያለ  ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሰላም የማስከበር ስራ የፀጥታ አካላት ብቻ አይደለም፤ ከጎናቸው በመሆን ዘብ ልንቆም ይገባል ነው ያሉት አቶ ታዬ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተወሰኑ አካላትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ የደህንነታችን ዋስትና ነው ያሉት ደግሞ በከተማዋ የአቢሲኒያ ሆቴል አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ላፋሞ ናቸው።

አስተዳዳሪው እንዳሉት ወደ ድርጅታቸው የሚመጡ እንግዶችን በቂ ፍተሻ በማድረግና በመታወቂያቸው በማየት እያስተናገዱ ናቸው፤ የፀጥታ አካላትም በየዕለቱ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ ነው።

"የሰላማችን ባለቤት እኛው ስለሆንን ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት በኃላፊነት መንፈስ እየሰራን ነው" ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አባል ሳጂን መሐመድ ቶሌራ በበኩላቸው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በወሳኝ ሰዓት መታወጁን  ተናግረዋል።

በውስጥና በውጭ ጠላቶች የተከፈተብን የህልውና ዘመቻ በድል ለመወጣት ከኅብረተሰቡ ጋር ተጣምረን በመስራታችን ውጤት እየተመዘገበ ነው ያሉት።

በዞኑ ከአሸባሪው  ህወሓት ጋር  ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ግብረ-ኃይል ሰብሳቢ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ ናቸው።

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት የኅብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑም ሁሉም ኅብረተሰብ ተደራጅቶ  አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

በአሸባሪው ህወሓትና ግብረ አበሮቹ የተጋረጠውን ወቅታዊ የሕልውና እና የሉዓላዊነት አደጋ ለመከላከል  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ተደንግጎ በመላው ሀገሪቱ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም