አሸባሪው ጉዳት ያደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ 30ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ጉዳት ያደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ 30ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ
ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) የማዕድን ሚኒስቴር አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ጉዳት ያደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ዛሬ የተረከቡት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎችን ጨፍጭፏል፤ የንብረት ዘርፏልና ውደመት ፈጽሟል።
ቡድኑ በክልሉ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብትና ንብረት ማውደሙን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው በስልጣን ዘመኑ ዘርፎ ባካበተው የህዝብ ሃብት መልሶ ሀገሩንና ህዝቡን በመውጋት አሳፋሪ ታሪክ መፈጸሙንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የጥፋት ቡድኑ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ በየግንባሩ እየተደቆሰ በመሆኑ በቅርቡ ይህ አስከፊ ጊዜ አልፎ ወደ ሰላም እንደምንመለስ ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለኝም ነው ያሉት።
ወራሪው ቡድን በክልሉ ህዝብና ንብረት ላይ ያደረሰውን ጉዳት የተረዱ ኢትዮጵያውያን እያሳዩ ላሉት ወገናዊ አጋርነት አድናቆታቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የማዕድን ሚኒስቴር ያደረገው ድጋፍ ለመልሶ ግንባታው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማመልከት በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ የአፋር ህዝብ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በመጠበቅ የአሸባሪውን ሀገር የማፍረስ ፍላጎት ቅዠት ሆኖ እንዲቀር የጉላ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
ለአፋር ጀግኖች አኩሪ ታሪካዊ ገድል ታላቅ አክብሮትና አድናቆት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ተቋማቸው ለዚህ ህዝብ ያለውን አክብሮትና አጋርነት ለመግለጽ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያሰባሰበውን 30 ሚሊዮን ብር ማበርከታቸውና በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።