"ፌደራሊስትና ኮንፌደራሊስት"- የአሸባሪው ህወሃት ሌላኛው መልክ - ኢዜአ አማርኛ
"ፌደራሊስትና ኮንፌደራሊስት"- የአሸባሪው ህወሃት ሌላኛው መልክ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2014/ኢዜአ/ እራሳቸውን "ፌደራሊስትና ኮንፌደራሊስት" በሚል የሚያደናግሩት ኢትዮጵያን በመበተን የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት የተዘጋጁ ሃይሎች መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካል ሳይንስና የሕግ ምሁራን ገለጹ።
በአሜሪካ ዘጠኝ አባላት ያሉት "የኢትዮጵያ ፌደራሊስትና ኮንፌደራሊስት" ኃይሎች በሚል የተጠራሩ ግለሰቦች "ተጣመርን" ሲሉ ሰሞኑን ታይተዋል።
የጥምረታቸው ዋነኛ ዓላማም የኢትዮጵያን መንግስት በሃይል በማውረድ ኢትዮጵያን በታትኖ ለራሳቸው ጥቅም መቀራመት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስና የሕግና ምሁራን ይገልፃሉ።
የጥምረቱ አባላት በብሔር ስም የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት የሚሯሯጡ የአፈንጋጭ ብሔርተኞች ስብስብና የአሸባሪው ህወሃት ሌላኛው መልክ መሆኑን ምሁራኑ ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት መምህር ኢያሱ ግዛው፤ "ተጣመርን" የሚሉት ሃይሎች ኢትዮጵያን አፍርሰው ለመቀራመት የተዘጋጁ ጥቅመኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
አክለውም "እነዚህ ድርጅቶች ኮንፌድራል ወይም ፌደራሊስት ሀይሎችም አይደሉም ትክክለኛ ስማቸው አፈንጋጭ ብሄርተኞች ነው " ብለዋል።
በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ሕግ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ፤ ጥምረቱ ሕወሃት መልኩን ቀይሮ በሌላ አቅጣጫ የመጣበት የጥቅመኛ ወንበዴዎች ጥርቅም መሆኑን ይናገራሉ።
እነዚህ ተጣመርን የሚሉ ሃይሎች ለሕዝብ ድምፅና ፍላጎት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ የጥቅመኞች ስብስብ መሆኑንም መምህር ኢያሱ አስረድተዋል።
ዶክተር አልማው በበኩላቸው ጥምረቱ በኢትዮጵያ ኮንፌደሬሽን ለመመሥረት የሚያድርጉት ጥምረት የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ያላደረገ፣ ያለፈበትና አገር የማፍረስ አንዱ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች የሚያደርጉትን ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ሊያስቆሙ ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።