ከአባቶቻችን በወረስነው ጀግንነት የአሸባሪውን ህወሓት ቡድን እንደመስሳለን---የባህር ዳር ከተማ ዘማቾች

ባህር ዳር ፣ህዳር 8/2014(ኢዜአ) ከአባቶቻችን በወረስነው ጀግንነት አሸባሪውን ህወሓት በገባበት ገብተን በመደምሰስ የሀገራችንን ሕልውና ለማስጠበቅ ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ዘማቾች ገለፁ።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትን  የክተት ጥሪ ተቀብለው ከባህር ዳር ከተማ ለሚዘምቱ የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላትና የህዝባዊ ኃይሎች ዛሬ ሽኝት ተደርጓል።

ወደ ግንባር የተሸኙት ምክትል አስር አለቃ ይበቃል እጅጉ እንዳሉት በቀድሞ መከላከያ ሠራዊት የአግዓዚ ኮማንዶ ክፍለ ጦር የቤተ መንግሥት ጥበቃ አባል ነበሩ።

በወቅቱ የህወሓት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ "የብሔር መመጣጠን" በሚል ምክንያት በተሰራባቸው ሸፍጥ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት አባልነት በክብር እንደተሸኙ ገልፀዋል።

"አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሀገራቸው ብዙ መስራትና ማገልገል የሚችሉ በርካታ የኮማንዶ አባላትን በማንነት ምክንያት እንዲሰናበቱ አድርጓል" ሲሉም አክለዋል።

አሸባሪው የህወሓት በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና ግድያ ለመከላከል የተደረገውን የክተት ጥሪ ተቀብለው እንደዘመቱም ተናግረዋል።


አቅም ያላቸው ወጣቶች ከሠራዊቱ ጋር በግንባር በመሰለፍ፤ አቅም የሌላቸውም በአካባቢያቸው የህብረተሰቡን ደህንነት እንዲያስጠብቁ አመልክተዋል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ የሚካሄደው ጦርነት ለሀገር ህልውና ሲባል መሆኑን አውቆ ለሀገሩ ዘብና መከታ ሊሆን እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

"ደጀኑ ህዝብም በየአካባቢው የዘማቾችን ቤተሰብ መንከባከቡን ሊያጠናክር ይገባል" ብለዋል።


ወጣት ቢታኒያ ቻሌ በበኩሏ ሀገር ከሌለች ምንም ነገር እንደማይኖር አምና ሀገሯን ወገኖቿን ለመታደግ የክተት ጥሪውን መቀበሏንና መዝመቷን ተናግራለች።

"ወራሪውና ከሀዲው የህወሓት ቡድን ሀገር እያወደመና በዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸመ ሳይ ሴትነቴ ሳይገድበኝ የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ በቁርጠኝነት ተነስቼያለሁ" ብላለች።

በአሸባሪው ህውሓት የተጋረጠውን ወቅታዊ የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እንደ ጀግኖች አርበኛ አባቶችና እናቶች የሽብር ቡድኑን በግንባር ተፋልማ አከርካሪውን ለመስበር ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

ሀገርን ለወራሪ ቡድን አሳልፎ ላለመስጠት ጠላት እኪደመሰስ ድረስ ትግሏን እንደምታጥናክርም ገልጻለች።    

''የቀድሞ አባቶቻችን የአድዋ ጦርነትን በድል እንደተወጡት ሁሉ ዛሬም እኔ ማሲንቆዬን ይዤ ዘምቻለሁ'' ያለው ደግሞ የማሲንቆ ተጫዋቹ መታገስ ማሩ ነው።

የቀረበውን የክተት ጥሪ ተከትሎ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች እንዲነሱ በማሲንቆው የቅስቀሳ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግሯል።

"ሀገር ሰላም ሲሆን ነው በማሲንቋችን ሰርተን የምንበላው" ያለው መታገስ፣ "እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ በየግንባሩ የተሰማራውን ሠራዊት በሙያችን ለማጀገን ዘምተናል" ብሏል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አደራ ጋሼ በበኩላቸው፣ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች የክተት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ግንባር መዝመታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ወራሪውን ህወሓት በአጠረ ጊዜ ለመደምሰስ የከተማው ወጣቶችና የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት መዝመታቸውን ተናግረዋል።

የከተማዋን ዘማቾች የሚያስተባብሩና የሚዋጉ 16 አመራሮች በግንባር እንዳሉ ገልፀው፣ ያልዘመቱ አመራሮችም የከተማዋን ፀጥታ የማስጠበቅና የስንቅ ዝግጅት ስራውን በማስተባበር እየደገፉ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም