ኮሚሽኑ ለተፈናቀዮች 26 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ለተፈናቀዮች 26 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ደብረ ብርሃን ፤ ህዳር 8/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በአሸባሪው ህወሓት ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ወገኖች 26 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ሀገር የገጠማትን ፈተና መሻገር የሚቻለው እርስ በርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የሚገጥሟትን ፈተናዎች ሁሉ የምታልፍባቸው መልካም እሴቶች እንዳሏት ገልፀው፤ "ሁሉም ዜጋ በመተባበር የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ሴራ ለማምከን መስራት ይኖርበታል" ብለዋል።
በጦርነቱ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮችም ኮሚሽኑ ካደረገው በድጋፉ ስኳር፣ ፓስታ፣ አልባሳት፣ ጫማና ሌሎች ቁሶች ይገኙበታል።
ድጋፉ ከደረሰው ጉዳት ስፋት አንፃር ሲታይ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በቀጣይም መሰል የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ለመግታት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
"አሸባሪው ከሸኔና ከውጭ አጋሮቹ ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የለኮሰው ጦርነት ቀድሞ እራሱን እያጠፋው ነው" ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልሎች ንጽሃንን በግፍ ከመጨፍጨፍ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማድረሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለችግር ተዳርገዋል።
ለእነዚህ ወገኖች አሁን ላለባቸው ወቅታዊ ችግር ከሚደረገው ድጋፍ ባለፈ በቀጣይ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ በመንግሥት በኩል እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
"ይህን ክፉ ጊዜ ለመሻገር መደጋገፍና መረዳዳት ይገባል" ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ፣ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደአማኑኤል በበኩላቸው፣ "የተደረገው ድጋፍ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያ ያለባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያቃልል ነው" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከ218 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ድጋፉ በፍትሃዊነት ለችግረኞች እንደሚሰራጭ ገልጸዋል።
በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሞቀ ቤታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ለችግር እንዳይጋለጡም የሚመለከተው ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
በድጋፉ ርክክብ ሥነሥርዓት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ሞላ እንዲሁም የፌደራልና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡