ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 8/2014 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር፤ አገሪቱ በህልውና ዘመቻ ላይ ብትሆንም ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ287 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፤ ከዚህም መካከል 156 ሚሊዮን የሚሆነው ከዲያስፖራ አባላት የተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበው ገንዘብ ከአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቦንድ ግዥና በድጋፍ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሕዝቡ በሕልውና ዘመቻ ላይም ሆኖ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን በማጠናከር ለግንባታው መጠናቀቅ ቁርጠኝነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
ግድቡ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሁሉም ዜጋ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚ እንዳትሆን ለሚሰሩ ሃይሎች እውነታውን የማሳወቅ ሥራም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጽህፈት ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ አቅዶ እየሰራ መሆኑ ታውቋል።