ቀጥታ፡

በውጭ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዘገባዎችን በንቃት መመከት ይገባል

ሐዋሳ፤ ህዳር 8/2014 (ኢዜአ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በባህር ማዶ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዘገባዎችን በንቃት ሊመክቱ ይገባል ሲሉ በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አመለከቱ።

ኢዜአ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/  የሲዳማ ዞን አስተባባሪ አቶ እንግዳውርቅ አሰፋ  እንደገለጹት አሸባሪዎቹ  ህወሓትና ሸኔ  በታሪካዊ የውጭ ጠላቶች በመታገዝ  ሀገር የማፍረስ አጀንዳቸውን ለማሳካት በሀገርና በህዝብ ላይ  አደጋ ደቅነዋል።

አሸባሪዎቹ  አለም አቀፍ መገናኛ ብዘሃንን  እንደ መሳሪያ በመጠቀምና ሀሰተኛ ዘገባ በማሰራጨት የሀገሪቱን ህልውና በመፈታተን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ህወሓትና ሸኔ  ሀገርን ለማፍረስ  ይጠቅማል ባሉት አማራጭ ሁሉ እየታተሩ መሆናቸውን የገለጹት አስተባባሪው፤ "ይህንን እውነታ መረዳት የተሳናቸው የምዕራቡ አለም መገናኛ ብዙሃን   የሀሰት መረጃ በመዘገብ የዓለም ማህበረሰብን እያሳሳቱ ነው" ብለዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የመገናኛ ብዙሃኑን የሀሰተኛ መረጃ ጦርነት ለመመከት የተለያዩ ቋንቋዎችን ተጠቅመው የሀገሪቱን እውነታ ከማስረዳት ባለፈ ለጉዳዩ ባላቸው ቅርበት ለአለምአቀፍ ማህብረሰብ እውነታውን በማስረዳት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር መርሆች ባፈነገጠ መልኩ ሚዛናዊነት የጎደለውና  ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ ዘገባ የሚያሰራጩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በመላው ዓለም የሚገኙ  ኢትዮጵያዊያን ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

''አንዳንድ ሀገራት የፈረሱትና ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ የደረሰባቸው በውስጣቸው በሚፈጠሩ ችግሮች ነው'' ያሉት አስተባባሪው፤ ይህ በሀገር ላይ እንዳይደርስ  በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ  ለሀገሩ ዘብ በመቆም ሀገርን ከጥቃት መከላከል እንዳለበት አመላክተዋል።

''ሀገር ለማዳን የሚደረግ ዘመቻ በፓርቲ አይገደብም'' ያሉት አቶ እንግዳወርቅ የፓርቲው አባሎችንም  ሆነ ማህበረሰብ ከመቀስቀስ  ባለፈ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

የሲዳማ አንድነት ፓርቲ  ሊቀመንበር አቶ ለማ ኦያቶ በበኩላቸው በአሸባሪው ህወሓት በሀገርና በህዝብ ላይ የተቃጣውን  ጦርነት  ለመመከት መላው የሀገሪቱ ህዝብ ካለምንም ልዩነት በአንድነት መቆሙ የሚደነቅ መሆኑን  ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ የሚታየው አንድነት እንዲጠናከር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ጎን በመቆም የህልውና ዘመቻውን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

በተለይም በውጭ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከመመከት አንጻር የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን  በኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩት ሴራ እየበረታ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ለማ፤ ይህን በሀገርና በህዝብ  ላይ የተደቀነው የህልውና አደጋ ለማክሸፍ በውጭ የሚኖረው ማህበረሰብ ባላቸው እውቀትና ችሎታ በመዝመት ግንባር ቀደም ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

''በሀገር ህልውና ማንም አይደራደርም'' ያሉት አቶ ለማ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች፣ የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች፣ አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት የኢትዮጵያዊያንን ፍላጎት ተረድተው ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንዲቆሙ በፓርቲው ስም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን ለመበተን የውስጥና የውጭ ሃይሎች የከፈቱትን ጦርነት ለመመከትና ለመቀልበስ መላው ዜጋ የጀመረውን  የተቀናጀ ትግል ከዳር ሊያደርስ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ   በነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሲዳማ ክልል ሰብሳቢ አቶ ታደለ ጠና ናቸው።

በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለህልውና ዘመቻ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ከሚያደርገው  አስተዋጽኦ ባሻገር ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀንና ሌሎችንም አማራጮች በመጠቀም ያለውን ተጨባጭ  እውነት ለመላው አለም ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሲዳማ ህዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራር  አቶ ደሳለኝ ዮታ  በበኩላቸው በስልጣን ጥም የሰከረው አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ የሸረበው ሴራ በቁርጥ ቀን ልጆች ማክሸፍ መቻሉን  አስታውሰዋል።

አሜሪካን ጨምሮ የሴራው ጠንሳሽና ተባባሪ የሆኑ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት እውነታውን ወደ ጎን በማለት  ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ለማሽመድመድና በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የአለምን ማህበረሰብ ለማደናገር የሚያደርጉት ተጨባጭ እንቅስቃሴ ያስተዛዝባል ብለዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን  ለመበተን የሚፈልጉ የውጭ ረዥም እጆችን ነቅቶ በመጠበቅና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሀገር  በማዳን ስራው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በውጭ የሚኖረው ማኅበረሰብ ኢትዮጵያን አስመልክቶ በውጭ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዘገባዎችን  በንቃት በመከታተልና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት  የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም