ቀጥታ፡

"ኮንፌደራል-ፌደራል" በሚል ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ ሴራ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ አካል ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 08 ቀን 2014 (አዜአ) በአሸባሪው ህወሃት መሪነት "ኮንፌደራል-ፌደራል" በሚል ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ ሴራ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ አካል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት በስልጣን በቆየባቸው ዓመታትም ሆነ በህዝቦች ትግል ከማዕከላዊ መንግስት ከተባረረ በኋላ  ኢትዮጵያውያንን በማባላት ሀገር ለማፍረስ ሴራዎችን ሸርቦ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያ ለእሱ ስትመች በጭቆና የሚገዛት፤ ካልሆነ ደግሞ አንድነቷ የተበታተነ ደካማ ሀገር እንድትሆን ረዥም ርቀቶችን ተጉዟል።

ኢትዮጵያውያን የአሸባሪ ቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ በተባበረ ክንድ በመመከት ረገድ አኩሪ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ናቸው።

አሸባሪ ቡድኑ መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖም "ፌደራል-ኮንፌደራል" በሚል ሽፋን ዓላማውን ለማሳካት ተስፋ የመቁረጥ መፍጨርጨር እያደረገ ይገኛል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች " ኮንፌደራል -ፌደራል" የሚለው የአሸባሪ ቡድኑ አካሄድ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ አካል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ኤፍሬም አሰፋ፤ በአሸባረው የህወሃት መሪነት በዋሽንግተን ዲሲ "ፌደራል-ኮንፌደራል" በሚል ስያሜ የተመሰረተው የግለሰቦች ስብስብ ኢትዮጵያን መንግስት አልባ በማድረግ አገር ለማፍረስ የተቀረጸ የፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ያለ ማንም ተጽዕኖ አገራቸውን አሸናፊ ያደረገ ምርጫ በማካሄድ የሚያስተዳድራቸውን መንግስት መመስረታቸውን ገልጸዋል።

በምርጫው ኢትዮጵያውያን መንግስት የመመስረት ሚናቸውን በሚገባ በመወጣት የሽብር ቡድኑን ፍላጎት ማክሸፍ ስለመቻላቸው አንስተዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ፕሮግራም ቀርጾ ወደ ትግል መግባቱን አስታውሰዋል።

በመላው ኢትዮጵያውያን ትግል የደርግ ስርዓት ከተገረሰሰ በኋላም አሸባሪው ህወሃት የአምባገነንነት ስርዓትን ዳግም በኢትዮጵያውያን ትክሻ ላይ መጫኑን ነው የተናገሩት፡፡

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ዘርግቶት የቆየው የጭቆና እና ዘረፋ ስርዓት ደግሞ የድርጅቱን ትክክለኛ ባህሪ የገለጸ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

አሸባሪ ቡድኑ በተግባር ያልተሳካለትን ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ በእጅ አዙር ለመሞከር እየጣረ መሆኑን ጠቅሰው፤ " ኮንፌደራል-ፌደራል " የሚለው አካሄድም የዚሁ አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ህዝቦች አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መጋቢ ብሉይ አብርሃም፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ አካላት የተፈጠረ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ መሪነት የ" ኮንፌደራል-ፌደራል" ጽንሰ ሃሳብን በቅጡ ያልተረዱ ግለሰቦች ስብስብ ፈጥረው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየዶለቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊያን ዳግም የከፋፍለህ ግዛ ፓለቲካዊ ስርዓትን የሚሸከም ትክሻ እንደሌላቸው አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ይህን ከፋፋይ ድርጅት ከእነ አስተሳሰቡ ለመቅበር በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም