አካባቢያችንን ከመጠበቅ ባለፈ መከላከያን ተቀላቅለን አሸባሪዎቹን ለመፋለም ወስነናል - ኢዜአ አማርኛ
አካባቢያችንን ከመጠበቅ ባለፈ መከላከያን ተቀላቅለን አሸባሪዎቹን ለመፋለም ወስነናል

ሐረር፤ ህዳር 8/2014(ኢዜአ) አካባቢያቸውን ነቅተው ከመጠበቅ ባለፈ መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል አሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔን ለመፋለም መወሰናቸውን የሐረሪ ክልል ወጣቶች አስታወቁ።
ወጣቶቹ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና የወጣቶች ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሐረር ከተማ አካሄደዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በክልሉ የአሚር ኑር ወረዳ ነዋሪ ወጣት ፈረሃን ቶፊቅ በሰጠው አስተያየት፤ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመው፣የህዳሴ ግድብን የተጻረረ እና በኢትዮዽያ አንድነት ላይ ጽንፍ የፈጠረው አሸባሪ ህወሃት እና ተላላኪዎቹ ናቸው ብሏል።
አሸባሪዎቹ በሀገሪቱ ላይ ምንም አይነት ጥቃት መፈጸም እንዳይችሉ ማድረግ የሚችለው ወጣቱ በመሆኑ ለዚህም የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ተደራጅተው የአካባቢያቸው ሰላም እያስጠበቁ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ የአባዲር ወረዳ ነዋሪ ወጣት መክፊራ ናስር ናት።
በተለይ በአሁኑ ወቅት የወረዳው ወጣቶች ለመዝመት ወስነው መነሳሳታቸውን አመልክታለች።
አሸባሪዎቹ የሚነዙትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እንደማትሰማ እና ሌሎችም በዚህ ተግባር እንዳይታለሉ መልዕክት አስተላልፋለች።
ወጣት ሙጀሂድ ረመዳን በበኩሉ፤ የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተን ሰራዊቱን የመደገፍ እና አካባቢን የመጠበቅ ስራዎች እያከናወን እንገኛለን ብሏል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ የትስስር ገፆች የሚለቀቁ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎች ለማክሸፍ የድርሻውን ከመወጣት ባለፈ ሰራዊቱን በመቀላቀል አሸባሪዎችን ለመፋለም መወሰኑን አስታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ወጣቶች የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ኦነግ ሸኔ ሀገር የማፍረስ ተግባር ለመመከት በሚደረገው ርብርብ ሚናቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
በተለይም በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የሚሰራጩ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በአግባቡ በመገንዘብ መታገል እንደሚኖርባቸው አመልክተው፤ ቡድኑን ማጥፋት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡