ቀጥታ፡

ማህበሩ በአሸባሪው ሸኔ ለተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ

ነገሌ፣ ህዳር 8/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጉጂ ዞን ሶስት ወረዳዎች በአሸባሪው ሸኔ ለተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች በጥሬ ገንዘብ 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሊበን ደበሶ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ጉሚኤልደሎ፣ ሊበንና ጎሮዶላ ወረዳዎች በአሸባሪው ሸኔ በተፈጠረ የሰላም እጦት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች በነገሌ ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከወረዳዎቹ ለተፈናቀሉ ለ3ሺህ 317 አባወራ አርብቶ አደሮች በጥሬ ገንዘብ የ40 የሚሊዮን ብር ድጋፍ  ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ ተፈናቃይ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ እያደረገ ስላለው ድጋፍ አመስግነው ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የነገሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዮሀንስ ፈይሳ በበኩላቸው ለተፈናቃይ አባወራዎች በቤተሰብ ብዛት ከ8 ሺህ እስከ 13ሺህ 300 ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ ቀደም ሲልም በአካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ ዘይትና እህል፣ የቀንና የሌሊት አልባሳት  እንዲሁም የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ከተፈናቃዮች መካከል የጉሚኤልደሎ ወረዳ ነዋሪ አቶ ድብት ሾባ የ15 ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ጠቁመው በማህበሩ ስለተበረከተላቸው 13ሺህ 300 ብር ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

"መንግስት የአካባቢው ሰላም ወደ ቀደመበት ተመልሶ ወደ መኖርያ ቀያችን ፈጥነን እንድንመለስ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይገባል" ሲሉ ጠይቀዋል።

"የሽብር ጥቃት፣ ስደትና መፈናቀል ለሴቶችና ለህጻናት ፈታኝ ነው" ያሉት ደግሞ በወረዳው የኦዳ መዴራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጡሜ ገባቦ ናቸው።

"የሽብር ጥቃት ቆሞ ሰርተን መኖር ካልቻልን እስከመቼ ነው እየተረዳን የምንኖረው የሚለው ያሳስበኛል" ያሉት ወይዘሮ ጡሜ "መንግስት ወንጀለኞችን አደብ አስገዝቶ በፍጥነት ወደ አካባቢያችን እንድንመለስ እንድንቋቋም  ሊያደርግ ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል።

በማህበሩ ስለተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም