በኢትዮጵያ የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትልን ማጠናከር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፣  ህዳር 8/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመውለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትልን ማጠናከር እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በየዓመቱ ህዳር 8 ቀን የሚከበረው የዓለም የመውለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ8ኛ ጊዜ ይከበራል።

እለቱ " ከመውለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ጨቅላ ህጻናት በሚደረገው እንክብካቤ ከወላጆቻቸው በፍጹም እንዳይለዩ አሁኑኑ እንተግብር" በሚል መሪ ሃሳብ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተከብሯል።

የብሔራዊ የጨቅላ ህጻናትና ጤና አስተባባሪ ሰለሞን ገበየሁ፤ በዓለም ላይ የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአለም ላይ በየዓመቱ በአማካይ ከ15 ሚሊዮን በላይ ጨቅላ ህጻናት የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ እንደሚወለዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።  

ከእነዚህ መካከል አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት የአንድ ወር እድሜ ሳሞላቸው እንደሚሞቱ ይነገራል።

በኢትዮጵያም በየዓመት በአማካይ ከ376 ሺህ በላይ ህጻናት የመውለጃ ቀናቸው ሳይደርስ ሲወለዱ ከ27 ሺህ የሚበልጡት የሚሞቱ መሆኑ ተገልጿል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም፤ ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ጨቅላ ህጻናት ላይ የሚያጋጥመውን ህመም፣ የአካል ጉዳትና ሞት መቀነስ ብሎም አካላዊና ስነ-ልቦናዊ  ክብካቤ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከተወለዱበት እለት ጀምሮ የሰውነት ሙቀታቸውን ለመጠበቅ፣ አተነፋፈሳቸውን እና የደም ዝውውርን ለማስተካከል እንዲሁም ለአጠቃላይ ጤንነታቸውና እድገታቸው ከወላጆቻቸው እንዳይለዩ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ የሚወለዱ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በጤና ተቋማት መውለድ እንዲሁም የቅድመ ወሊድ እና የድህረ ወሊድ ክትትልን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

ለጨቅላ ህጻናት ህመሞች አፋጣኝ ህክምና እና እንክብካቤ መስጠትም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።   

በኢትዮጵያ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር መሰረት፤ አሁን ላይ 196 የሚሆኑ ሆስፒታሎች ጽኑ የጨቅላ ህጻናት ህክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አክለዋል።

2 ሺ 900 የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ደግሞ የጨቅላ ህጻናት ክብካቤ ኮሪደር ኖሯቸው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም