ዳያስፖራው የጀመረውን ጥረት የአሜሪካን ሕዝብ ማዕከል ባደረገ መልኩ ይበልጥ ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው የጀመረውን ጥረት የአሜሪካን ሕዝብ ማዕከል ባደረገ መልኩ ይበልጥ ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፣ ህዳር 8/2014(ኢዜአ) በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ የጀመሩትን ጥረት የአሜሪካን ሕዝብ ማዕከል ባደረገ መልኩ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ ።
አቶ አርጋው አየለ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ከአሜሪካዊት የትዳር አጋራቸው አምስት ልጆችን ያፈሩት አቶ አርጋው ለጊዜው ኑሯቸውን በኢትዮጵያ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ አቤኔዘር የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመው ወገኖቻቸውን እየረዱ ሲሆን በቅርቡም የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል በመሆን አገራቸውን እያገለገሉ ነው።
አቶ አርጋው በቅርቡ አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ የምታራምደውን አቋም በመቃወም በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር እውነታውን ለማስረዳት እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።
እርሳቸውን ጨምሮ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እያደረጓቸው የሚገኙ ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን፤ ሆኖም አሁንም በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በተለይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መቀመጫ በሆነው ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት ከሚካሄዱ ሠላማዊ ሠልፎች ባሻገር የተደራጁ ይፋዊ እንቅስቃሴዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በየግዛቶቹ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሚወክሏቸው የሴኔትና የኮንግረስ አባላት ቢሮ በመሄድ የኢትዮጵያን እውነታ ማስረዳትና መሞገት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው ያሉት አቶ አርጋው የአሜሪካን ሕዝብ እና መንግሥት መለየት ይገባል ብለዋል።
ስለ ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት እንጂ የአሜሪካ ሕዝብ የተሳሳተ አቋም አልያዘም የሚሉት አቶ አርጋው ይህንን ለመቀየር እውነታውን ለሕዝቡ መንገርና ማስረዳት ይገባል ብለዋል።
አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በማኅበራዊ ሚዲያ የአገራቸውን እውነታ ለማስረዳት የሚያደርጉት ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ይሁንና በማኅበራዊ ሚዲያ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚተላለፉ መልዕክቶች ከስድብ የጸዱና ዓላማቸው እውነታውን ማስገንዘብ ላይ ብቻ ያተኮሩ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ አርጋው መንግሥት በኢትዮጵያ ለሚገኙ አሜሪካዊያን እውነታውን በማስረዳት የሁለቱ አገራት ወዳጅነት እንዳይበላሽ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ነው የተናገሩት።