ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ በጥቅምት ወር ከ53 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የገቢዎች ሚኒስቴር በጥቅምት ወር ከ53 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

ገቢው የተሰበሰበው በሀገሪቱ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት 4 ቅርንጫፎች ምንም ሳይሠሩ እና በሌሎችም ቢሆን በተገደበ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁኖ የተሰበሰበ በመሆኑ አፈፃፀሙ የተሻለ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው ገልጸዋል።

የጥቅምት ወር ዕቅድ 56 ቢሊዮን 588 ሚሊዮን 899 ሺህ 862 ብር ከ73 ሳንቲም መሆኑን የገለጹት አቶ ላቀ፤ በወሩ 53 ቢሊዮን 906 ሚሊዮን 833 ሺህ 456 ብር ከ85 ሳንቲም በመሰብሰቡ አፈፃፀሙም 95.26 ነው ብለዋል።

ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በብር 9 ቢሊዮን 657 ሚሊዮን 313 ሺህ 974 ከ68 ሳንቲም ወይም 21.82% ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል።

ገቢው የተሰበሰበው ከሀገር ውስጥ ታክስ 42 ቢሊዮን 67 ሚሊዮን 793 ሺህ 289 ብር ከ29 ሳንቲም፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ ደግሞ 11 ቢሊዮን 839 ሚሊዮን 40 ሺህ 167 ብር ከ56 ሳንቲም እንደሆነ አሳውቀዋል።

አሰባሰቡ የተሻለ የሆነበት ግብር ከፋዮች ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው በማሰብ በወቅቱ እና በትክክለኛው ጊዜ ግብራቸውን አሳውቀው በመክፈላቸው ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

በሌላ በኩል የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞች ከምንጊዜውም በቁርጠኝነት እና በትጋት ከልብ መሥራት በመቻላቸው እንደሆነም አክለዋል።

የገቢ አሰባሰቡ ስኬታማ እንዲሆን አበርክቶ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡት የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው፣ በቀጣይም ሀገርን በጋራ ለማሻገር በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።

-አካባቢህን ጠብቅ

_ ወደ ግንባር ዝመት

_ መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም