ቀጥታ፡

ለሀገር ሉአላዊነት መከበር መስዋትነት መክፈል ክቡር በመሆኑ ለዚህም ቁርጠኞች ነን - የቀድሞ ሰራዊት አባላት

ዲላ ፤ ህዳር 8/2014 (ኢዜአ) ለሀገር ሉአላዊነት መከበር የሕይወት መስዋትነት መክፈል ክብር በመሆኑ ለዚህም ቁርጠኞች ነን ይላሉ ከደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን መከላከያን ለመቀላቀል የተዘጋጁ የቀድሞ ሰራዊት አባላት።
 አባላቱ የመንግስት ጥሪ በመቀበል አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለማጥፋት እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ለመሳተፍ  መወሰናቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

 ወታደር ከበደ ዲዶዋቆ ለዘመቻው ከተዘጋጁት የቀሞ ሰራዊት አባላት መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ አሸባሪው ህወሓት ሀገር ከመድፈር ባለፈ በአፋርና አማራ ክልሎች በንጹሀን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙ እንዳስቆጣቸው ነው የተናገሩት።

ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ በግንባር ተፋልመው የቡድኑን አስከፊ ተግባር ከማስቆምና ከማጥፋት በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ እንዳይሳካ እናደርጋለን ብለዋል።

ልጃቸው የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑን ያወሱት ወታደር ከበደ፤  ለሀገር ሉአላዊነት መከበር የሕይወት መስዋዕትነት መክፈል ክብር በመሆኑ ለዚህም ዝግጁና ቁርጠኛ ነኝ ነው ያሉት።

በተለይ ልጄና ጓዶቼ እየተፋለሙ እኔ ቤት መቀመጤ አግባብ ባለመሆኑ የመንግስትን ጥሪ ተቀብዬ  በድጋሜ ለመዝመት ወስኛለሁ ብለዋል።

እንደ ቀድሞው ሁሉ አስፈላጊውን መሰዋዕትነት በመክፈል በድል ለመመለስ  በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔ መነሳሳታቸውን አስታውቀዋል።

አሸባሪውን የህወሃት ቡድንን በመቅበር ሀገር ወደ ሰላሟ እስከምትመለስ  ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን በቆራጥነት ለመፋለም መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የቀድሞ ሰራዊት አባል ወታደር ተፈሪ ጠሮ ናቸው።

ቡድኑ ቀድሞውንም ቢሆን በሌብነትና በማጭበርበር እንደሚታወቅ አስታውሰው፤ በግንባር በመፋለም ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

አስር አለቃ ሃይሉ ጉቴ በበኩላቸው፤ የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን በተለያዩ ግንባሮች ለሀገራቸው ክብር መዋደቃቸውን አስታውሰዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን ከውጭ ወራሪዎች ጋር ተዋድቀው በክብር ያስረከቡንን ሀገር ህወሀት እንዲጫወትበት መፍቀድ የለብንም ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ከውስጥና ከውጭ ሀይሎች ጋር በማበር የከፈተብንን ወረራ በመመከት እንደ አባቶች ነጻ ሀገር ለልጆቻቸው ለማውረስ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የሽብር ቡደኑን በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ በግንባር  በመሰለፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

የዞኑ ህዝብ በዓይነትና ገንዘብ  በተደጋጋሚ ድጋፍ ከማድረጉ ባለፈ አመራሩን ጨምሮ በርካታ ልጆቹን የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባላትንና ተጠባባቂ ሀይሉን ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ ማመቻቸቱን  የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ ናቸው።

የህወሓት የሌብነትና የግፍ አገዛዝ ዳግም እንዳይመለስ የዞኑ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ሁሉን አቀፍ  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም