ቀጥታ፡

ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በዓለማችን በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ሊካሄድ ነው

ህዳር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እና ጫና የሚቃወም ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በዓለማችን በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ላይ የፊታችን እሁድ ሕዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

ሰልፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ጎን መቆሙን የሚያሳይበትም ነው ተብሏል።

የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ከባዱ ሙሉቀን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሰልፉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉ በመተባበር ድምጻቸውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያሰሙበት ነው፡፡

በሰሞኑ በዋሺንግተን ዲሲ፣ ቶሮንቶ እና ብራሰልስ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገቡ ሰልፎች መካሄዳቸውን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ በማሰብ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ሰልፍ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ዋሺንግተን ዲሲ፣ አትላንታ፣ ኒውዮርክ፣ ቶርንቶ፣ ካልጋሪ፣ ጆሀንስበርግ፣ ቴልአቪቭ፣ ቶኪዮ፣ ሲድኒ፣ ለንደን፣ ኮሎራዶና ቺካጎ እሁድ ሰልፎቹ ከሚካሄድባቸው ከተሞች መካከል ይገኙበታል።

በዕለቱ ሰልፍ የሚካሄድባቸው ሌሎች ከተሞች በቀጣይ ቀናት ይፋ እንደሚሆኑ አቶ ከባዱ ጠቁመዋል።

የየከተሞቹን የጊዜ አቆጣጠርን መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ በየከተሞቹ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፉ ሰልፍ አካል የሆነው ተቃውሞ በሞንትሪያል እና በኦቶዋ ከተሞች ቅዳሜ ሕዳር 11 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲሁም በናሽቪል ከተማ ሕዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ከተማ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።

ሕዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም በጄኔቫ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ሰልፉ ምዕራባውያኑ የሚያደርጉትን ጫናና ጣልቃ ገብነት ከማውገዝ ባለፈ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚያስተለልፏቸውን የሐሰት ዘገባዎች እንዲያቆሙ የሚያሳስቡ መልዕክቶች እንደሚተላለፍበት ገልጸዋል።

በውጪ አገር የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ጋር አንድ መሆኑን እንደሚያሳዩም ነው አቶ ከባዱ ያስረዱት።

በሰልፉ ላይ የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉና በተለያዩ ተወካዮች አማካኝነት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን እውነት እንዲሰማና ጣልቃ ገብነቱ እንዲቆም ግፊት ማድረጉን ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ለኢትዮጵያ ሕልውና መጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም እንዲሁ።

ሕዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምና አንድነት ማህበር የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል፣የ#NoMore የትዊተር ዘመቻ እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች፣ የተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳድ ወዳጆች በጋራ እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም