ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የምትኖረው በልጆቿ መስዋዕትነት በመሆኑ ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለን ለመዝመት ተነስተናል - ዘማች አመራሮች

ህዳር 7/2014(ኢዜአ) " ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የምትኖረው በልጆቿ መስዋዕትነት በመሆኑ ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለን አገራችንን ከወራሪ ኃይል ለመጠበቅ በፈቃዳችን ለመዝመት ተነስተናል" ሲሉ ከደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተውጣጥተው ወደ ግንባር የዘመቱ አመራሮች ገለጹ፡፡
ከደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተውጣጥተው ወደ ግንባር ላመሩ አመራሮች በቡታጅራ ከተማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽኝት አድርገውላቸዋል፡፡

ሽኝት የተደረገላቸው አመራሮች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉትም ''በእኛ መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች።''

"አገራችንን ከውስጥና ከውጭ ባንዳ ለመከላከል በቁጭትና ጽናት ተሰልፈናል" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የሰው ሃብትና ሥራ አመራር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈለቀ ናና ተቋም መምራትና አገልግሎት መስጠት የሚቻለው ቅድሚያ አገር ስትኖር በመሆኑ አገራቸውን ከወራሪ ኃይል ለመታደግ በግንባር ለመዝመት መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪውን ቡድን እስከወዲያኛው ለማስወገድም የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡   

የከንባታና ጠንባሮ ዞን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተመስገን ማርቆስ በበኩላቸው እኔ እያለሁ አገሬ እንደማትፈርስና እንደማትበተን ለሚመለከተው ሁሉ ለማሳወቅ ነው በወኔ ለመዝመት የተዘጋጀሁት ብለዋል፡፡

ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ የሚገኙ አካላትን እኩይ ሴራ ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው እንደሚመክቱም ተናግረዋል፡፡

ለመንግሥት ጥሪ ሁሉም ምላሽ መስጠት አለበት ያሉት አቶ ተመስገን፤ አካባቢን በመጠበቅ፣ መከላከያን በመደገፍ እና በአካል በመዝመት አገርን ማገልገል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

 የሀደሮ ጦንጦ ዙሪያ ወረዳ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ማትዮስ ወልደሬ ደግሞ አገር በአሸባሪ እየተወረረች ቆሜ አላይም ብዬ ነው የምዘምተው ብለዋል፡፡  

በግንባር በመገኘትም አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ከመከላከያው ጋር በመሆን አገሬን እጠብቃለሁ ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

"ኢትዮጵያን ለማቆየት አባቶቼ ትናንት የፈጸሙትን ገድል በመድገም ለመጭው ትውልድ የተከበረች ሀገር ለማስረከብ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ተነስቻለሁ" ያሉት ደግሞ የከንባታ ጠንባሮ ዞን የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ተመስገን አማረ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያዊያንን አንገት ለማስደፋት የተነሳውን አሸባሪ ኃይል መክተው ለመመለስና ዳግም ለኢትዮጵያ ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እንደሚታገሉም ገልጸዋል፡፡

"በአካል ዘምቼ ለአገሬ ነጻነት ዘብ ለመቆም ስወስን በታላቅ ደስታና ጀግንነት ነው" በማለትም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም