ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምትቀጥለው በ'ጅረት' በሚመሰል የትውልድ ቅብብሎሽ ነው

አዲስ አበባ፣  ህዳር 7/2014 (ኢዜአ)   የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚቀጥለው በ'ጅረት' በሚመሰል የወጣቱ ትውልድ ቅብብሎሽ መስዋዕትነት ነው ይላሉ የፍልስፍና ምሁሩ ዮናስ ዘውዴ።

ኢትዮጵያ 70 በመቶ ሕዝቧ ወጣት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዮናስ፤ ወጣት ደግሞ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከትና በአካል ይገለጻል ይላሉ።

ኢትዮጵያ እንደ ጅረት በሚፈስ የትውልድ ቅብብሎሽ ከአባቶችና ቅድመ አያቶች የቀጠለች አገር እንደሆነች ገልጸዋል።

በአድዋም ሆነ በሌሎች የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ማስጠበቂያ ጦርነቶች መስዋዕትነት በመክፈል አገር እንድትቀጥል ካደረጉት መካከል የወጣቱ ሚና የላቀ ድርሻ እንደሚይዝ አንስተዋል።

ዛሬም ኢትዮጵያ ከተደቀነባት የነጻነት፣ የግዛት አንድነትና የሉዓላዊነት አደጋ የመታደግ ጉዳይ በይበልጥ በወጣቱ  ላይ የተጣለ ኃላፊነት መሆኑን ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ታሪክ ባንዳነት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ገልጸው፤ ዛሬም በውጭ ሃይሎች የሚጋለቡት የሸኔና የትህነግ የሽብር ቡድኖች ኢትዮጵያን ለማፍረስ በባንዳነት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን አፍርሼ ታላቋን ትግራይ እመሰርታለሁ ቢልም፤ የኢትዮጵያ ወጣት ደግሞ አትፈርስም ይልቁንም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች በሚል ተጋድሎ እየፈጸመ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን የመጣችበት መንገድ አባጣ ጎርባጣ ቢሆንም በወጣቶች የትውልድ ቅብብሎሽ መስዋዕትነት እየተከፈለ ሕልውናዋ ተጠብቆ መዝለቁን አውስተዋል።

ምንም እንኳን አገር በምዕራባዊያን ኃይሎች ጫና እና በውስጥ ባንዳዎች እየተፈተነች ብትሆንም፤ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ካስጠበቁ ሁሌም ያሸንፋሉ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ወሳኙ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫጫታ ሳይሆን ውስጣዊ ትብብርና አንድነትን አጠናክሮ፤ ጠላትን ተጋፍጦ መጣል ነው ይላሉ አቶ ዮናስ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም