ቀጥታ፡

የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለውን የተሳሳተ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ማስተካከል አለበት

ህዳር 7/2014/ኢዜአ/  የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለውን የተሳሳተ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያስተካክል የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበራት በአውሮፓ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበራት በአውሮፓ ለአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በጻፈው ደብዳቤ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው ግትር የፖሊሲ አቋም በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጿል።

"የዴሞክራሲያዊ ቅቡልነትና ሕጋዊነት ለአውሮፓ ሕብረት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ትርጉም አልባ እስኪመስል ድረስ አሸባሪው ሕወሓት የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ያሉ ወንጀሎች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ግትር አቋም ይዟል" ሲልም ነው የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበራት በደብዳቤው የገለጸው።

የባይደን አስተዳዳር በቅርቡ በዋሺንግተን ዲሲ በሕዝብ የተመረጠ መንግስትን በሃይል እገለብጣለሁ ብሎ ጥምረት ለመሰረቱ "የተበታተኑ የተቃዋሚ ቡድኖች" ድጋፍ መስጠቱ በኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀ  የጦርነት ዘመቻ መክፈቱን በግልጽ ያመላከተ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የልማት እርዳታ እንዳይሰጥ ማገዱ ዜጎችን ተጎጂ የሚያደርግ መሆኑንና አሁንም ሕብረቱ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እጥላለሁ ማለቱ ተቀባይነት እንደሌለው አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በሚመለከት ባደረጋቸው ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ሕብረቱ ከአሜሪካና ከሌሎች አገራት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አገርን ለማሳጣት ያደረገው እንቅስቃሴ አግባብ አለመሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ በጋራ ባወጡት ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳልፈጸመና ረሃብ ለጦር መሳሪያነት አለማዋሉን ቢያረጋግጡም አሁንም የምዕራባውያን አገራት ጫና በርትቶ መቀጠሉን ማህበራቱ አስታውቀዋል።

"አሸባሪው ሕወሓት ምዕራባውያን አገራት በዝምታቸው በሰጡት እውቅና ተጠቅሞ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ወረራ ፈጽሟል" ነው ያሉት ማህበራቱ ለፕሬዝዳንቷ በላኩት ደብዳቤ።

በቅርቡ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት አሸባሪው ሕወሓት በሁለቱ ክልሎች በፈጸመው ወረራ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ መግለጹን አውስቷል።

"አሸባሪው ሕወሓት ጥላቻ ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ የፈጸማቸው ድርጊቶች በጦር ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው" ብሏል።

የአሸባሪው ሕወሓት ድርጊቶች ለሰብአዊነት ቅንጣት ያክል ግድ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ የሚገልጸው ደብዳቤው የአውሮፓ ሕብረት ቡድኑ የፈጸመውን ተግባር አለማውገዙ እንዳሳዘነው ገልጿል።

በርካታ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት እና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተቀናጀ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት መረጃ ጦርነት የምዕራባውያን ኢትዮጵያን የማጥላላት ስትራቴጂ አካል መሆኑንም ነው ማህበራቱ ለፕሬዝዳንቷ በደብዳቤያቸው ላይ ያመለከቱት።

በዚህም እውነታን በመሸፋፈን፣ነገሮችን በማጋነንና የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መከራን ለመጨመር እና የኢትዮጵያን መንግስት ተቀባይንት ለማሳጣት እየሰሩ ነው ብሏል።

አብዛኞቹ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ምክንያታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ድምጾችን እና የኢትዮጵያን አቋም የሚያንጻባርቁ ሀሳቦችን ዝም ለማስባል ቆርጠው የተነሱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የአሸባሪው ሕወሓትና ወኪሎቹን መርዛማ መልዕክቶች እያስተላለፉ መሆናቸውን አስገንዝቧል።

"ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ታማኝ አጋር እንጂ ጠላት አይደለችም፤ስለዚህም የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መቆም አለበት" ሲል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት በአውሮፓ ለህብረቱ ፕሬዝዳንት ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያ የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥና መሆኑን የጠቀሰው የማህበራቱ ደብዳቤ፤ በተለያዩ መስኮች እየተካሄዱ ያሉ ማሻሻያዎች ደግሞ  ኢትዮጵያ ለገጠሟት ፈተናዎች ዘላቂ መፍትሔ ያመጣሉ ብሎ እንደሚያምንም ነው ያስታወቀው።

አሸባሪው ሕወሓት ስልጣን ላይ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የፈማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ነጻና ገለልተኛ በሆነ መልኩ በመመርመር ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብና ለተጎጂዎች ፍትሕ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነም አመልክቷል።

ይህን በማድረግ የተሻለ ነገን በኢትዮጵያ ማምጣት እንደሚቻልም ነው ያብራራው፡፡

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሌይን በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት በአውሮፓ  ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም