አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች የሚያሰራጩት የሀሰት ዘገባ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ አካል ነው - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች የሚያሰራጩት የሀሰት ዘገባ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ አካል ነው
ህዳር 7/2014/ኢዜአ/ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች የሚያሰራጩት የሀሰት ዘገባ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ አካል መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ገለጹ፡፡
ስመ-ጥር የሆኑ አንዳንድ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት በተደራጀ መልኩ የሀሰት ዘገባዎችን እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡
ለአብነትም እነዚህ ሚዲያዎች “የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም የዘር ማጥፋት እየፈጸመ እንደሆነ” አስመስለው የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ ባደረጉት የጥናት ሪፖርት መሰረት ውንጀላው መሰረተ ቢስ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ራስን በልማት የመቻል አካሄድ የማይፈልጉ ሀገራት የሚዘውሯቸው ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀ የሀሰት ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
እነዚህ ሚዲያዎች ከጋዜጠኝነት መርህ ባፈነገጠ መልኩ ምንጩ የማይታወቅና ምናባዊ ድርሰት የሚመስል ዘገባ እንደሚያሰራጩም ነው ያብራሩት፡፡
እነዚህ ሚዲያዎች አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች እያደረሰ ያለውን ግፍና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሞ ሲያነሱት እንደማይታይም ነው የተናገሩት፡፡
በተቃራኒው "አዲስ አበባ ተከባለች" የሚል እና ሌሎች መሬት ላይ ያለውን ሀቅ የሚክዱ ዘገባዎችን በመስራት ህዝብን ለማደናገር በተጨባጭ ሲጥሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያውያን እንዳይረጋጉ በማድረግ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልእኮ አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው የሚዲያ ዘመቻ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በአራት ቀናት ብቻ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ በርካታ የሀሰተኛ ዘገባዎች "ስመ-ጥር" በተባሉ የምእራባውያን ሚዲያዎች ተሰራጭተዋል ብለዋል፡፡
ከሚዲያዎች በተጨማሪ አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያወጧቸው መረጃዎች ዘመቻው የተቀናጀ መሆኑን እንደሚያመላክት አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በሚዲያዎች በሚሰራጩ ሀሰተኛ ዘገባዎች ሳይደናገሩ ሀገራቸውን ነቅተው መጠበቅ እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ሁሉም ዜጋ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ለመመከት ዝግጁ መሆን እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡