ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት አይቻልም

ህዳር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ችግር በውጪ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሊፈታ እንደማይችል እና መፍትሄው ከውስጥ መምጣት እንዳለበት የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ አምባሳደሮች አምባሳደር ቲቦር ናዥ እና አምባሳደር ዶናልድ ቡት ተናገሩ።

አምባሳደሮቹ የዘር መከፋፈል ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር እንደዳረጋት ገልፀው፤ “ኢትዮጵያውያኖች ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድነትና በሰላም መኖር የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው” ብለዋል።

በኢትዮጵያና በጊኒ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በትራምፕ አስተዳደር ረዳት የውጭ ጉዳይ የነበሩት ቲቦር ናዥ እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ እና ዛምቢያ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ቡት ኢትዮጵያውያን ለውጪ ሀይል ግፊት የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማስተዋላቸውንና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚና ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ካሮል ካስቲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሲተገበር የኖረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር መሰረት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ችግር የተባባሰው የፖለቲካ አመራሮች ከህዝቡ ድጋፍ ለማግኘት ዘርን መጠቀማቸው ነው ያሉት አምባሳደር ቡት፤ በኢትዮጵያ የተሞከረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት የታሰበውን ውጤት አለማምጣት ለዚህ ልዩነት መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳደረገ አስምረውበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አድርገዋቸው የነበሩ የፖለቲካ መሻሻሎች በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ነበሩ ብለዋል አምባሳደር ናዥ።

በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ላለው ግጭት አዎንታዊና አሉታዊ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ዲፕሎማቶቹ፤ የኢትዮጵያ ችግር ከመሰረቱ እንዲፈታ ኢትዮጵያኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ስለወደፊታቸው መነጋገር አለባቸው ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ውጪ ያለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለኢትዮጵያ መሆን አለበት ብለው የሚያስቡትን አቅጣጫ ከማዘጋጀት ይልቅ፣ ህዝቡ በራሱ ችግሮቹን መፍታት የሚችልበትን መንገድ በማመቻቸት ብቻ እንዲያግዝ አሳስበዋል።

አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም