የሀገሬን ነጻነት በማረጋገጥ ወደ ሙያዬ መመለስን መርጫለሁ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገሬን ነጻነት በማረጋገጥ ወደ ሙያዬ መመለስን መርጫለሁ
ህዳር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ጠላትን ድል በመቀዳጀት የሀገሬን ነጻነት ለማረጋገጥ ወደ ሙያዬ መመለስን መርጫለሁ" ይላሉ ሠልጣኝ መምህሩ።
መምህር ዘመኑ ታረቀኝ ከአዊ ብሔረሰብ ዞን ወደ የአማራ ልዩ ኃይል ለመቀላቀል ዛሬ ወደ ማሰልጠኛ ከተሸኙ ዜጎች መካከል አንዱ ናቸው።
ኢትዮጵያ በሰፈር ወራሪ መደፈሯ ስላሳሰበኝ የመምህርነት ሙያየን ለጊዜው ወደ ጎን በመተው ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ አሻራ ለማሳረፍ ወደ ስልጠናው ማቅናት ወድጂያለሁ ብለዋል መምህር ዘመኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት።
"በዚህ ወቅት ክልሌና ሀገሬን ከወራሪው ጠላት ጥቃት ነጻ እንዲወጡ ወታደራዊ ስልጠና ወስጄ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ጠላትን ድል በመቀዳጀት የሀገሬን ነጻነት በማረጋገጥ ወደ ሙያዬ መመለስን መርጫለሁ" ይላሉ።
ሀገርን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪና ወራሪው የህወሃት ቡድን ለመፋለም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተንቀሳቀሱ ዜጎች ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ የቀሩም ኢትዮጵያዊያን ያጋጠመውን የህልውና አደጋ በመረዳት ራሳቸውን በማሰልጠን ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
በቆይታቸው በሚያገኘው ወታደራዊ ስልጠና ወራሪውንና የውስጥ ባንዳዎችን ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ማጽዳት ላይ እንደሚያተኩር መምህር ዘመኑ አስታውቀዋል።
ወጣት ግዛቸው ሰዋገኝ በበኩሉ፤ ከሥልጠና በማገኘው ዕውቀት ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ ወራሪውንና የጥፋት ተላላኪዎችን በመደምሰስ ክልሉንና ሀገሪቱን ነጻ ለማውጣት ቁርጠኛ መሆኑን ይናገራል።
ሀገሬ ወራሪው ከደቀነው የህልውና አደጋ ነጻነቷን ለማወጅ እየተጣራች ባለችበት በዚህ ወቅት ከሥልጠናው ወጥቼ የድርሻዬን ለማበርከት ወደ ማሰልጠኛ በመሄዴ ደስተኛ ነኝ ብሏል።
በኢትዮጵያ ህልውናና ሉዓላዊነቷ ላይ የመጡና ለመምጣት የሚመኙ ካሉ ለመመከት በሚካሄደው ትግል በመሳተፍ እስከ መስዋዕትነት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ፤ ከሀገር የሚቀድም ስለማይኖር ለጠላት ክፍተት መስጠት እንደማይገባ ነው የጠቆመው።
ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመውጋት የተነሳው ወራሪውና አሸባሪው ህወሃትን ከሀገር መከላከያ ጋር በመሆን በመደምሰስ ዳግም እንዳይነሱ ለማድረግ ወደ ልዩ ኃይል ስልጠና መቀላቀሉን የገለጸው ደግሞ ሌላው ወጣት አብርሃም መንግስቴ ነው።
ወራሪውን ከኢትዮጵያ ምድር በማጥፋት ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ በዚህ ወቅት ከዚህ በላይ ሌላ ጉዳይ የሚቀድም እንደሌለም ነው ወጣቱ የተናገረው።
የአዊ ብሔረሰብ ዞን የሠላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢሻው፤ ከአካባቢው ወደ ማሰልጠኛ ያቀኑት ዜጎች ካጠናቀቁ በኋላ ከሀገር መከላከያ፣ ልዩ ሀይልና ከሚሊሻና ፋኖ ጋር ተቀናጅተው እስከመጨረሻው በመፋለም የሀገርን ህልውናን የማስጠበቅ አደራ አለባቸው ነው ያሉት።
ሰልጣኞቹ ወራሪው ቡድን በሀገር ላይ የደቀነውን አደጋ በመቀልበስ በተለያዩ የመንግስት ተልዕኮዎች በመሰማራት ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ሰልጣኞቹ የሀገር ክብር በማስቀደም በፈቃዳቸው ወደ አማራ ልዩ ሀይል ሥልጠና እየገቡ ያሉት ለዘጠኛው ዙር መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከውጭ ጠላት ጋር በመተባበር በሀገራችን ላይ በፈጸመው ጥቃትና ደባ የተቆጡ ኢትዮጵያዊያን ከደጀንነት እስከ ግንባር ድረስ ተንቀሳቅሰው ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ እየሰጡ ያሉት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህም በደጀንነት ገንዘብ፣ ሰንቅና ሌሎችንም የሎጀስቲክስ ድጋፎች፤ በግንባር ደግሞ ወጣቶችና ሴቶች ሰልጥነው እንዲሁም የቀድሞ ሠራዊት አባላት፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በመዝመት የመከላከያ ሠራዊቱን በሰው ሃይል እያጠናከሩ ለሀገራቸው ያላቸው ቀናኢነት፣ ፍቅርና ክብር በተግባር በማሳየት ነው።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!