ወታደርም የውስጥ አርበኛም ሆነን የኢትዮጵያን ህልውና እናስቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
ወታደርም የውስጥ አርበኛም ሆነን የኢትዮጵያን ህልውና እናስቀጥላለን
አዲስ አበባ፣ ህዳር 06/2014 (ኢዜአ) ወታደርም የውስጥ አርበኛም ሆነን የኢትዮጵያን ህልውና እናስቀጥላለን ሲሉ በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የየካ ክፍለ ከተማ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ፅህፈት ቤት ተደራጅተው ከሚያመርቱ የሼድ አንቀሳቃሾች ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያ አገር ሆና እንዳትቀጥል በማሴር የተለያዩ የጥፋት ተግባራትን እየፈፀመ መሆኑን አንስተዋል።
"ኢትዮጵያን ማፍረስ" የሚል ግልጽ ጦርነት አውጆና የጥፋት ሃይሎችን አስተባብሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ሁላችንም ወታደርም የውስጥ አርበኛም ሆነን የኢትዮጵያን ህልውና እናስቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የአሸባሪውን አጀንዳ ለማሳካት በስውርና በግልጽ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ተላላኪዎች በዙሪያችን ሊኖሩ ስለሚችሉ መከታተልና ተጠያቂ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።
በየካ ክፍለ ከተማ በርካታ የመስሪያ ሼዶች ምክንያታቸው ሳይታወቅ መዘጋታቸውን ጠቅሰው አልፎ አልፎ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች የተለያዩ እቃዎችን ሲያከማቹባቸው ታዝበናል ብለዋል።
የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፀሃይ ኪባሞ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ጋር የሚያብሩ አካላት ለክህደት የተሰለፉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም በመስሪያ ሼዶች አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ክፍለ ከተማው የመለየት ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በግልጽም ይሁን በስውር የሽብርተኞች ደጋፊ የሆኑ አካላትን በፍጥነት ማጋለጥ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት በጸጥታ አካላት ብቻ የሚጠበቅ ባለመሆኑ የማህበረሰቡ ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።