የኢትዮጵያ አየር መንገድ በውጤታማነቱ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በውጤታማነቱ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 06/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጠንካራ የስራ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተገለጸ።
የአየር መንገዱ የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ተገምግሟል።
የስራ አፈጻጸም ግምገማውን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ አየር መንገዱ ባመጣው ትርፍና እድገት ጠንካራ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሩብ ዓመቱ በመንገደኞችና በጭነት ማጓጓዝ ካስመዘገበው አመርቂ ውጤት በተጓዳኝ በፕሮጀክት አፈጻጸም፣ ከአፍሪካ አገራት ጋር ባለው የቢዝነስ ትስስር እና ውስጣዊ አስተዳደሩን ቀልጣፋ በማድረግም ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ አየር መንገዶች በኪሳራ በሚንቀሳቀሱበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጤት ማስመዝገቡ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
የደንበኞችን እርካታ ከፍ ወዳለ ደረጃ በማድረስ የድርጅቱን አፈጸጸም ይበልጥ ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ለሚያደርገው ትስስርና ቅንጅትም የገንዘብ ሚኒስቴር ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ የአየር መንገዱ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ወጪ ቆጣቢ አሰራር በመተግበራቸው ውጤታማ አፈጻጸም ሊመዘገብ ችሏል ብለዋል።