ቀጥታ፡

የባይደን አስተዳደር ከተሳሳተ ፖሊሲ ወጥቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ሊሰራ ይገባል

አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኛ ከሆነች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ ከተመረጠው መንግሥት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የህግ ምሁር የሆኑት ዶክተር ዘውድነህ በየነ አስገነዘቡ።

ምሁሩ ባስነበቡት ጽሁፍ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማስቀጠል አሜሪካ ልባዊ ፍላጎት ካላት የባይደን አስተዳደር የሚከተለውን የተሳሰተ ፖሊሲ ዳግም ሊቃኝ ይገባል።

የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለከፋ ሰቆቃ እየዳረገ ካለው አሸባሪ የህወሓት ቡድን ጎን ከመቆም ወጥቶ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በህዝብ ከተመረጠው መንግሥት ጋር በጋር ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የትኛውም የውጭ ፖሊሲ አሸባሪውን ህወሓት እንደ ጠቃሚና ለትግራይ ህዝብ ብቸኛ ጠባቂ አድርጎ ማሰቡ ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር የህወሓትን የዘር የበላይነት ትርክተ ታሪክን መመርመር እንዳለበት አስገነዝበዋል።

በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በግልጽም ይሁን በስውር ይህንን አካሄድ የሚያበረታታ ፖሊሲ በእርግጠኝነት የኢትዮጵያን አለመረጋጋት ያራዝመው እንደሆን እንጂ እልባት አያስገኝም ነው ያሉት ዶክተር ዘውድነህ።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ለጆ ባይደን የፕሬዚዳንትነት ዘመቻ እና ዴሞክራቶች በምርጫው እንዲያሸንፉ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዶክተር ዘውድነህ አስታውሰዋል።

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ለሚከተሉት ፖሊሲ ረቂቅ ሲያዘጋጁ ድጋፍ ያደረጉላቸው ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንን አለማማከራቸው ዲያስፖራውን ማሳዘኑን ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሂደት ተፈጥሯዊ ሚዛኗን ጠብቃ ትቀጥላለች” ያሉት ዶክተር ዘውድነህ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዳይ ለሕዝቧ መተው ግን አማራጭ የሌለው መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

ዳሩ ግን በቂ ባልሆነ መረጃና ባልተገባ ፖሊሲ የሚቀርቡ የመፍትሄ ሃሳቦችን አስገዳጅ በሆነ መልኩ ገቢራዊ ለማድረግ መሞከር የህዝቡን ሰቆቃ ከማራዘም ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው አስረድተዋል።

እናም አሉ ዶክተር ዘውድነህ “የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የተፈጠረው ቀውስ እልባት እንዲያገኝ ካሰበ ካለፈው አንድ ዓመት አንስቶ መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለውን የተሳሰተ ፖሊሲ በቅድሚያ ሊያጤነው ይገባል” ብለዋል።

የአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ላዩን ሲያዩት ግልጽና በግጭቱ ሰለባ የሆኑትን የሚደግፍ ቢመስልም ነገር ግን ዓውዱን በሚገባ ያልተረዳና ግንዛቤ የጎደለው ነው ብለውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም