ከ60 በላይ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከ60 በላይ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ህዳር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከ60 በላይ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢዋን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
በኮሚሽኑ የኤክስፖርት ፕሮጀክቶች ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር ሳሙኤል አሰፋ፤ ኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርቷን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እያደረገች ያለውን ጥረት አብራርተዋል።
በዚህም የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ከ60 በላይ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ላይ መሆኗን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶች ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ኤዥያና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተላኩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የገበያ ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የወጪ ንግድን ለማሳደግ የሚያስችል ጥናት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥናቱ የገበያ አማራጭን ከማስፋት በተጨማሪ ከአንዳንድ አገራት የሚደርሰውን ያልተገባ ጫና በመቋቋም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚመረቱ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት በማስተዋወቅ ገበያ እንዲያገኙ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ሳሙኤል የገለጹት።
የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአይነትና በመጠን በማሳደግ እንዲሁም የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በወጭ ንግድ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ከተወጡ በዘርፉ የሚፈለገውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻልም አብራርተዋል።
በተለይም የማዕድን ዘርፉ በታቀደው ልክ ከተሰራበት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሬ ታገኝበታለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በርካታ ሃብቶች ያሏት ቢሆንም ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ያሉት ምርቶች አነስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ “በቀጣይ ብዙ መስራት ይጠበቃል” ብለዋል።
የወጭ ንግድንና የገበያ ተደራሽነትን ለማሻሻል ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በያዘችው የ10 ዓመት የልማት እቅድ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሌሎች መስኮች ላይ በማተኮር በየዓመቱ በአማካይ 10 በመቶ እድገት የማስመዝገብ እቅድ እንዳላት ይታወቃል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣_
መከላከያን ደግፍ።