የኢትዮጵያ ልጆች ድምፅ በአሜሪካ ከዶክተር መላኩ በያን እስከ ዛሬ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልጆች ድምፅ በአሜሪካ ከዶክተር መላኩ በያን እስከ ዛሬ ቀጥሏል
የኢትዮጵያ ልጆች ድምፅ በአሜሪካ ከዶክተር መላኩ በያን እስከ ዛሬ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ በባዕዳን በየዘመናቱ ተፈትናለች። የፈተና ጉዞዋን ግን በልጆቿ መስዋዕትነት ተሻግራ ዛሬ ደርሳለች። የጥቁሮች የነጻነት ቀንዲል በመሆኗ የተነሳ ቂም የያዙባት ምዕራባዊያን የቅኝ ግዛት አራማጆች ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለመድፈር ለዘመናት ኳትነዋል። ለዚህ ግባቸውም ቅጥረኛ ባንዳዎችን ተጠቅመዋል። ያም ሆኖ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነውና ጡትና እጇን የነከሱ ልጆች እንዳሏት ሁሉ በየዘመናቱ በምጥ ስትያዝ ያዋለዷት፣ ለሕልውናዋ የተሰዉላት ብርቅዬ የቁርጥ ቀን ልጆችም አጥታ አታውቅም። ከልጆቿ ባለፈም ከኢትዮጵያ ጋር ወግነው ድምጽ የሆኗት አያሌ የቁርጥ ቀን ወዳጆችም አፍርታለች።
ከአድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈጽም ኢትዮጵያዊያን ክተት ብለው ተነስተው ለአገራቸው ተጋድለዋል። የፋሺስት ጦር በሰው ልጆች ላይ የተከለከለ ጅምላ ጨራሽ መርዝ ተጠቅሞ ለጊዜው ድል የተቀዳጀ ቢመስለውም ኢትዮጵያዊያን ለአምስት ዓመታት ዱር ቤቴ ብለው ነጻነቷን አረጋግጠዋል። በወቅቱ ኢትዮጵያ በድሕረ አንደኛው ዓለም ጦርነት የተመሰረተው የመንግስታቱ ማህበር(ሊግ ኦፍ ኔሽን) ይህን የግፍ ወረራ ያስቆመዋል ብላ ስሞታ ብታቀርብም አልተሳካም። ይባስ ብሎም ኢትዮጵያ ከውጭ የገዛችውን የጦር መሳሪያ እንዳታስገባ በማኅበር ማዕቀብ ተጣለባት። ኢትዮጵያ በግፍ ስትወረር አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባዊያን ጥቅማቸው ነውና ለማውገዝ ከቶውንም አልሞከሩም። ዓለም ፊቱን ያዞረባት ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ የተባበረ ክንድ ሉዓላዊነቷን አስከብራለች።
በዚህ የግፍ ወረራ ወቅት ከአርበኞቿ ተጋድሎ ባሻገር በኃያላን አገራት የሚኖሩ የፀረ-ቅኝ ግዛት ታጋይ የቁርጥ ቀን ልጆችም ነበሩ። ከነዚህም መካከል በሀገረ-አሜሪካ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተማሪ ዶክተር መላኩ በያን አንዱ ነበሩ።
ዶክተር መላኩ በያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኦጋዴን ጠላትን ተዋግተዋል። የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ምሩቁ ዶክተር መላኩ በያን ፋሺስት ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር በሚኖሩበት አሜሪካ "ፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ማፋፋም አለብን" በሚል የመላው ዓለም ጥቁሮችን ቀሰቀሱ። ስለ ኢትዮጵያ ማንነትና የዘመናት ተጋድሎ ለአፍሮ-አሜሪካዊያን ተዘዋውረው ሰበኩ።
ከጎናቸውም በርካቶችን አሰለፉ። የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ፋና ወጊዎች ማርክስ ጋርቬይን መሰል የጥቁር መብት አቀንቃኞችን አስተባብረው ምዕራባዊያን ቅኝ ግዛትና ጭቆና ላይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ አበረታቱ።
በአሜሪካ 'የኢትዮጵያዊያን ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን' የተባለ ድርጅት መሰረቱ። ከአንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ጋር ትዳር የመሰረቱት ፓን አፍሪካዊው መላኩ በያን ያቋቋሙት 'የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕብረት' ከማርክስ ጋርቬይ ''የጥቁሮች ዓለም አቀፍ ለውጥ ማህበር እና የአፍሪካ ማህበረሰብ ሊግ" ከተሰኘው ድርጅት ጋር ይመሳሰል ነበር። "እኛ የተነሳነው የተባበሩት አፍሪካን ለመመስረት ነው" በሚልም ሰፊ ቅስቀሳ አድርገዋል። (በእነዚህ አይነት ንቅናቄ እርሾዎች ላይ ከ23 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረቱን ልብ ይሏል)።
መላኩ በያን "የኢትዮጵያ ድምፅ- ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ጋዜጣ በመመስረት ስለአገራቸው ጮኸዋል። የወቅቱን የፋሺስት ኢጣሊያ ግፍና ሰቆቃዎች አጋልጠዋል። ጥቁሮችን አሰባስበውም ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ በማድረግ ለኢትዮጵያ አርበኞች ድጋፍ ማሰባሰብም ችለዋል። አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛትና ባርነት ቀንበር ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁም ጥቁሮችን አነሳስተዋል።
ለነፃነት ቁልፉ ጉዳይ የአፍሪካዊያን አንድነትና ትብብር ስለመሆኑ ወትውተዋል። የኢትዮጵያ ወዳጆችንም አፍርተዋል። ለአብነትም የእውቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ወላጅ እናት ሲልቪያ ፓንክረስት " new times and ethiopian times" የተሰኘ ጋዜጣ መስርተው በለንደን ለኢትዮጵያ ነጻነት ድምፅ ሆነዋል። (እኒህ ወጣትና ትልቅ ፓን አፍሪካዊ ምሑር ዶክተር መላኩ በያን ገና በ40 ዓመታቸው ኢትዮጵያ ነጻነቷን ልትቀዳጅ አንድ ዓመት ሲቀራት ነበር ያረፉት)።
የምዕራባዊያን ሴራና ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ዛሬም አልተለወጠም። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን ለማዳከም ለዓመታት ጥረዋል። በጥረታቸውም ኢትዮጵያ ጠል ስብስብ የሆነውን የሕወሃት ተገንጣይ ቡድን ወደ ሥልጣን በማምጣት ኢትዮጵያዊያንን እንዲከፋፍል፣ እንዲዘርፍና የአገር የጋራ እሴቶች እንዲያጠፉ በማድረግ በቀጣናው የፍላጎታቸው መጠቀሚያ ወኪል አደርገው ተጠቅመውበታል።
በአሜሪካና በሌሎች የምዕራብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮያዊያን ግን ይህን ፀረ-ኢትዮጵያ የባንዳ ኃይል ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለሦስት አሥርት ዓመታት ሙሉ እንደ መላኩ በያን በሰልፍና በዲፕሎማሲ ታግለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በመላ ኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በመኮነንና በፀረ-ዴሞክራሲ ሥርዓትን በማውገዝ ጫና እንዲደረግበት ቢወተውቱም ለራሳቸው ፍላጎት እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነትና ዕድገት የማይገዳቸው ምዕራባዊያን ትኩረት አልሰጡትም።
ዳሩ ግን ይህ አረመኔ ቡድን በህዝብ ማዕበል ከሥልጣን ከተወገደ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲሰራ በተቃራኒው በተለያዩ ውሃ ቀጠነ ጉዳዮች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫናውን አበረቱ። በተቃራኒው ለሽብር ቡድኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
ዛሬም ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ቡድን ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ በማበር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን የአገር ሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ከአገራቸው ጎን ቆመው አሸባሪውን ቡድን ማውገዛቸውንና የኢትዮጵያን እውነታ ማሳወቃቸውን ቀጥለዋል። የቁርጥ ቀን ልጆች ላለፉት ሦስት ዓመታት 'ኢትዮጵያን ማንበርከክ አፍሪካን ማንበርከክ ነው' ብለው የሚያምኑትን ምዕራባዊያንን ባላቸው አቅምና አጋጣሚ ሁሉ ሲሞግቱ በገሃድ ታይተዋል።
በተለይም በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ በምርጫ ያላቸውን ፖለቲካዊ መብት እና በዲፕሎማሲው ረገድ ሚናቸውን ተጫውተዋል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍን ጨምሮ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመደገፍ እንደ ዶክተር መላኩ በያን ለአገር አለኝታነታቸውን አሳይተዋል።
የተባበሩ ኢትዮጵያዊያን ድምፅ በርግጥም የአሜሪካንን መንግስት እየመራ ባለው ጆ ባይደን የዴሞክራቶች ፓርቲ ፖለቲካ ላይ ኪሳራ ማድረስ ስለመጀመሩ ከሰሞኑ ተስተውሏል። ይህም በድምፅ ካርዳቸው ዴሞክራቶችን መቅጣት ነው።
ዋሽንግተን ፖስት የተሰኘው ታዋቂና አንጋፋ ጋዜጣ ትላንት ይዞት በወጣው ዘገባ ኢትዮጵያዊያን የሪፐብሊካንን ዕጩዎችን ለመምረጥ፣ ዴሞክራቶችን አሽቀንጥሮ ለመጣል ምን አነሳሳቸው ሲል ያትታል። ለሁለት አሥርት ዓመታት በሰሜን ቨርጂኒያ ግዛት ነዋሪ የሆኑትን ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ግርማ መኮንን ያናገረው ጋዜጣው ለረጅም ጊዜ የዴሞክራቶች ደጋፊ እንደነበሩና፤ ዳሩ በዚህ ዓመት የ52 ዓመቱን ጊሌን ያንግኪን የተባለውን የሪፐብሊካን ተመራጭ ስለመምረጣቸው ይገልጻሉ።
ምክንያታቸው ደግሞ ዴሞክራቶች የባይደን አስተዳደር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያለው የተሳሳተ አቋም ስለመሆኑ ያብራራሉ። ይህም በተለይ ኢትዮጵያዊያንን ራሳቸውን ከዴሞክራት ደጋፊነት እንዲያገሉና ሪፐብሊካኖችን እንዲደግፉ ሰበብ ሆኗል ይላሉ። ሌሎች ኢትዮ-አሜሪካዊያንም በተመሳሳይ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ግጭቶች እንዲባባሱ የያዘችው ስህተት አካሄድ ተቃውመዋል።
የእነዚህ ኢትዮጵያዊያን ድምጾች የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም በኢኮኖሚ ማዕቀብ እና በነጻ ንግድ ተጠቃሚነቷ(አግዋ)ን ማቋረጥ ብሎም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መንግስት አፍርሶ የጨቋኙን የህወሓት ሥርዓት ለመመለስ ያለመ ነው የሚል ድምፅ እያስተጋቡ እንደሆነ ጋዜጣው ያትታል።
የኢትዮ-አሜሪካን ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (American-Ethiopian Public Affairs Committee-AEPAC) ሊቀ-መንበር መስፍን ተገኑ በበኩላቸው፤ የባይደን መንግስት አካሄድ አመክንዮ የጎደለው በመሆኑ ቁጣቸውን በዴሞክራት ፓርቲ ላይ ማሳረፍ እንደጀመሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አስተባባሪዎች በተደራጀ ሰላማዊ ሰልፍ የሪፐብሊካኑን ዕጩ በመደገፍ ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
በድምጻቸውም የሚፈልጉትን መምረጣቸውን ተከትሎ የኢትዮ-አሜሪካዊያን ድልም በሌሎች አካባቢዎች ለሚመረጡ የዴሞክራት ዕጩዎች ምርጫ ትልቅ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ስለመሆኑ ጋዜጣው ጽፏል።
ይህ ኢትዮ- አሜሪካዊያን ስብስብ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር እንድትሻገር የወቅቱን መንግስት መደገፍ እንጂ ማዳከም እንደማይገባ ለበርካታ ወራት ለበርካታ ኮንግረስ አባላት ደብዳቤ ማስገባታቸውን አቶ መስፍን ገልጸው፤ ነጩ ቤተ-መንግስት ግን ጫናውን ስለማበርታቱ ገልጸዋል። የባይደንን አስተዳደር የሚኮንኑ ሌሎች ሰላማዊ ሰልፎችም ዋሽንግተንን ጨምሮ በሌሎች የግዛት ከተሞች እንደሚደረጉ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
የሪፐብሊካን ተመራጩ ያንግኪንም የቨርጂኒያ ግዛት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል። በተለይም በቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ በክርና ጥለት ግብዓቶች እንዲሁም በኤሌክትሪካል መሳሪያዎች ረገድ የንግድ ግንኙነታቸውን በርግጥም በጥልቀት ልንሰራበት ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አድቮኬሲ ቦርድ አባል ገነት ንጉሴ በበኩላቸው፤ የዴሞክራት ዕጩ ቴሪ ማይክሊፍ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ አደረጃጀቶችን ተደጋጋሚ ጥሪ ከቁብ እንዳልቆጠሩ ገልጸዋል።
ከ35 በላይ የኢትዮ-አሜሪካዊያን ቡድኖች በግዛቷ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በያንግኪን ምርጫ ድጋፍ እና በባይደን ወገንተኛና የተዛባ ፖሊሲ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እንዲገልጹ መልዕክት መለዋወጣቸውን አትቷል። የዴሞክራት ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪዎችም ሁኔታው የዴሞክራት ተመራጮች የትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ፍላጎትና የልብ ትርታ መረዳትና ማሳተፍ እንዳለባቸው ብዙ የተማሩበት ስለመሆኑ፤ ወደፊትም ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ስለመገንዘባቸው ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።
የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ እንደሚያስረዳው የኢትዮጵያ ልጆች ከተባበሩ በአገር ቤት ብቻ ሳይሆን ድምጻቸው በምዕራብ አገራትም ዋጋ አለው። በአሜሪካ የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይላትን የመቃወም ተጋድሎ ከ80 ዓመታት በፊት በዶክተር መላኩ በያን ጀምሮ እስከ ዛሬም ቀጥሏል፤ ወደፊትም የተናበበና ኢትዮጵያን የማዳን ተጋድሎን የማጠናከር ሥራ ከቤት እስከ ባሕር ማዶ ይጠይቃል።