በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዋነኛ መንስኤው አሸባሪው ህወሃት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዋነኛ መንስኤው አሸባሪው ህወሃት ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6/2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያውያንን አብሮነት እና በሰላም መኖር የማይፈልገው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋነኛ ምንጭ ነው" ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ ክንዳቸው አሸባሪው ሕወሓት የደቀነውን ስጋትና አደጋ እየቀለበሱት ነውም ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ መቀመጫውን በሕንድ ዴልሂ ካደረገው "ዲዲ ኢንዲያ" ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
ዶክተር እዮብ በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመረዳት መንስኤውን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ስልጣን የመጣው መንግስት ፖለቲካና ኢኮኖሚን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ እርምጃዎች መውሰዱን ጠቅስዋል።
በተለይም በፖለቲካው ዘርፍ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሰራ ጠንካራ የፌዴራሊዝም ስርዓት መገንባት የሚያስችሉ ስራዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት መከናወናቸውን አመልክተዋል።
"የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃነትና ያሉ ልዩነቶችን እንደ እሴት በማየት አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ አገር የመገንባት ግብ ያለው ነው" ብለዋል ዶክተር እዮብ።
የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት እና በሰላም መኖር አጥብቆ የሚጠላው አሸባሪው ህወሃት እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ መኖር የለባትም" ብሎ ለማፍረስ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ሕወሓት ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን በመፍጠር በሕዝብ እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው የጥፋት ተላላኪዎችን ሲመክቱ መቆየታቸውን አንስተው አሸባሪው ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ላይ መጣሉን አመልክተዋል።
ጥቃቱ አሁን ላለው ግጭት መነሻ መሆኑንና በጥቃቱ በርካታ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ መሞታቸውን ገልጸዋል።
ችግሩን ተከትሎ መንግስት በወሰደው እርምጃ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አሸባሪው ሕወሓት የደቀነውን ስጋት ቀልብሶ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት እና አስፈላጊውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለትግራይ ሕዝብ ሲያቀርብ መቆየቱን አብራርተዋል።
"መንግስት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተጠናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል ቢወጣም ጫካ ገብቶ የሸፈተው የሕወሓት ቡድን የተኩስ አቁሙን ተገን አድርጎ በአፋር እና አማራ ክልሎች ወረራ ፈጽሟል" ብለዋል።
አሸባሪው ሃይል በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰዎችን በመግድል፣ አስገድዶ በመድፈር እና የንብረት ዝርፊያና ውድመት በማድረስ የጭካኔ ተግባር ፈፅሟል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል እየፈጸመ ያለው ወረራ በኢትዮጵያ ላይ የሕልውና አደጋና ስጋት ፈጥሯል፤ ይሄንንም አደጋ እና ስጋት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሆኖ እየቀለበሰው ይገኛል ብለዋል ዶክተር እዮብ።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሸባሪው ሕወሓት የደቀነባትን አደጋ ቀልብሳ የልማት፣ እድገትና የዴሞክራሲ ሕልሞቿን የማሳካት ጉዟዋን በአጭር ጊዜ ትመለሳለች ብለዋል።
"ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያላቸው ከሕወሓት ታጣቂ ቡድን ጋር ብቻ አይደለም፤ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውጭ ሃይሎች የሚደግፉትን የውክልና ጦርነት ጭምር ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት ከዚህ ቀደምም ሰርቶ አያውቅም አሁንም አይሰራም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ በቅርቡ ይሄን ጦርነት አሸንፋ ወደ መደበኛ ስራዋ እንደምትመለስ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንና የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ከልብ ከሚፈልጉ አጋሮች ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንዲፈታ እያደረጉ ያሉትን ጥረት መንግስት እንደሚደግፈውም ነው ዶክተር እዮብ የገለጹት።
አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያያዙትን አድሏዊ አቋምና ገንቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን በማቆም ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በውል ተረድተው ሰላም እንዲመጣ በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
"እነዚህ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብን ጨምሮ ሌሎች አፍራሽ እርምጃዎች በመውሰድ የሚፈጥሩት ለውጥ የለም፤ በሕዝብ የተመረጠን መንግስት ሕጋዊነት ለማሳጣት የሚደረገው ጥረትም ተቀባይነት የለውም ነው" ያሉት ዶክተር እዮብ።
ምዕራባዊያን አገራት ከኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ጎን በመሆን አሁን ላለው ችግር የመፍትሔ አካል እንዲሆኑና በኢትዮጵያ ላይ የወሰዱትን ያልተገባ እርምጃ ዳግም እንዲያጤኑ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት አቅም አላት፤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር አለበት በሚል በመርህ ላይ ተመስርታ ህንድ ያሳየችው አቋም መንግስትና ሕዝብን ማስደሰቱን ገልጸዋል።
ሕንድ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆሟ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር ያላት ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የመከራ ጊዜ ተሻግራ የእድገትና የብልጽግና ጉዞዋን እንደምታስቀጥል ዶክተር እዮብ አረጋግጠዋል።