ትውልዱ የአገሩን ህልውና በማስጠበቅ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜው አሁን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ የአገሩን ህልውና በማስጠበቅ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜው አሁን ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6/2014 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ የአገሩን ህልውና በማስጠበቅ እንደ ቀደምት አባቶቹ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣት የስፖርት ቤተሰብ አባላት ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
የስፖርት ለሰላም ማህበር አባል የሆነው ወጣት ናትናኤል የስፖርት ቤተሰቡ የመከላከያ ሰራዊቱን በመደገፍ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ የሚጥል ወረራ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑን ጠቅሶ፤ ኢትዮጵያውያን አባቶች በአደዋ፣ ማይጨውና ካራማራ ጠላትን አሳፍረው ኢትዮጵያን ማቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ደግሞ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማንበርከክ እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
እነዚህ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጭምር ጣልቃ እየገቡ መሆኑን አንስቶ፤ የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደምት አባቶቹ የራሱን የድል ታሪክ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማህበር አባል የሆነው ወጣት ምንያህል ጌታቸው በበኩሉ የህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያን ጠብቆ የማቆየት ትግል መሆኑን ገልጿል፡፡
በመሆኑም እኛ ወጣቶች አንድነታችንን ጠብቀን ለሀገራቸው ህልውና መጠበቅ ከፊት መሰለፍ አለብን ነው ያለው፡፡
በተጨማሪም ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም መጠበቅና ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን መሆን እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡
"አገራችን ከእኛ የምትጠብቀውን እውነተኛ መስዋእትነት ከፍለን ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ የምናደርግበት ጊዜው አሁን ነው" ያለው ደግሞ የስፖርት ባለሙያው ወጣት ማስረሻ ሞላ ነው።
ከዚህ አኳያ ወጣቱ ትውልድ በህልውና ዘመቻው ንቁ ተሳታፊ በመሆን የራሱን የታሪክ አሻራ ማስቀመጥ አለበት ብሏል፡፡
ወቅቱ አገር የተጨነቀችበት በመሆኑ የኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በጋራ መታገል እንደሚገባም ነው የተናገረው፡፡