ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 06/2014 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እወርዳለሁ በማለት ግልጽ መልእክት አስተላልፎ ከሌሎች የውስጥ ካሃዲዎችና የውጭ ሃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል።

አሸባሪ ቡድኑ የክህደት እርምጃውን የጀመረው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አገር ጠባቂውን ሰራዊት በማጥቃት መሆኑ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የአገር ክህደት ከመፈፀሙ በተጨማሪ በሰራዊቱ አባላት ላይ አሰቃቂ ድርጊት በመፈፀም አረመኔያዊነቱን አሳይቷል።

ይህንን አገር የካደ ሃይል ተጠያቂ ለማድረግ መንግስት ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ ገብቶ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን ማከናወኑ አይዘነጋም።

ከዚህ በኋላም ለትግራይ ህዝብ የተረጋጋ ህይወትና ሰብአዊ ተደራሽነትን የተመቻቸ ለማድረግ ሲል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም የአሸባሪው እኩይ ተግባር ግን እስካሁንም ሊቆም አልቻለም።

በአማራና አፋር ክልሎች በየደረሰባቸው አካባቢዎች በርካታ ጥፋቶችን እየፈፀመ፣ ንብረት እየዘረፈና እያወደመ እንዲሁም ንጹሃንን እየገደለ አገር የማፍረስ ተልእኮውን ለማሳካት እየሰራ ይገኛል።

በመሆኑም ይህንን አገር አፍራሽና ወራሪ ሃይል ለመመከት ኢትዮጵያዊያን በመዝመት፣ በመመከትና በመደገፍ አገራዊ አደራቸውን እየፈፀሙ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባም ወጣቶች በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ተመሳሳይ ተግባር እየፈፀሙ መሆኑን ተመልክተናል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶችም አካባቢያችንን ነቅተን ከጠበቅን አገር ተጠበቀች ማለት ነው ይላሉ።

ወጣቶቹ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ወጣት አያሌው ታደለም ያረጋገጠው ይህንኑ ነው።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለመበታተን በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ለመመከት ተዘጋጅተናል ሲል አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ህልውና በታሪክ አጋጣሚ በዚህ ትውልድ እጅ ላይ ይገኛል ያለው ሌላው አስተያየት ሰጭ እዮብ አሰፋ ክብሯን እና ልእልናዋን አስጠብቀን ልናስቀጥላት ግድ ይላል ብሏል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተዘጋጀውን አሸባሪ ሃይል በጋራ ክንዳችን በመመከት ድል ማድረግ አለብን ብሏል።

በፋሽስቶች ያልተንበረከከች፣ በቅኝ ግዛት ያልተያዘችና የጥቁሮችን አሸናፊነት ያረጋገጠችው ኢትዮጵያ በከሃዲዎች የተጋረጠባትን የህልውና ፈተና ተጋፍጠን ማሸነፍ አለብን ነው ያለው።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዘዳንት ገዛኸኝ ገብረማርያም፤ በመዲናዋ ሰላም በማስጠበቅ ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ተናግሯል።

በርካታ ወጣቶች ወደ ግንባር በመዝመትና ሰራዊቱን በመቀላቀል፣ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ ደም በመለገስና ሌሎችንም መልካም ተግባራት በመፈፀም አርአያነታቸውን እያሳዩ መሆኑን ገልጿል።

አሸባሪው ህወሃት ጠመንጃ አንስቶ ከከፈተው ጦርነት በተጨማሪ በተላላኪዎቹ አማካኝነት በተለይም በከተሞች የተለያዩ አሻጥሮችን ለመፈፀም እየሞከረ መሆኑን ያስታወሰው ገዛኸኝ አጠቃላይ ማህበረሰቡና በተለይም ወጣቶች እየመከቱት መሆኑን ተናግሯል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች በየአካባቢያቸው በመደራጀት ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው ለከተማዋና ለህዝቡ ሰላም እየሰሩ መሆኑን አብራርቷል።

አሸባሪው ህወሓት በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ህዝብን ለመረበሽና ስነ ልቦናን ለመሸርሸር እየጣረ ቢሆንም ፈፅሞ ሊሳካለት አይችልም ብሏል።

ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የማህበሩ ፕሬዘዳንት ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም